ለአፍሪካ ተምሳሌት ከሆነ ምርጫ እስከ መንግሥት ምሥረታ - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ተምሳሌት ከሆነ ምርጫ እስከ መንግሥት ምሥረታ
✍️ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ ፤ታላቅ ርዕይ
የአፍሪካ ቀንድ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካዊ ውጥረት፣ በግጭትና በተቋማዊ ድክመት የተፈተነ አካባቢ ነው። በዚህ አካባቢ ምርጫን በሰላም ማካሄድ፣ የሕዝብን ድምፅ ማክበር፣ ውጤትን በተቋማዊ መንገድ ማስተናገድ እና ወደ ሕጋዊ መንግሥት ምሥረታ መሸጋገር እጅግ ትልቅ ትርጉም አለው። የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በዚህ ረገድ ለአፍሪካ የሚያስተላልፈው መልዕክት ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማት መፍጠሯን፣ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በነጻነት ይበጀናል ያሉትን መንግሥት መምረጣቸውን፣ በዚህም በኃይል ሥልጣን ለመያዝ የቋመጡ አካላትን ሴራ ማክሸፋቸውን አሳይቷል።
ኢትዮጵያ ነገ የምትጀምረው አዲስ ምእራፍ ከሕዝብ ድምፅ ወደ ሥልጣን፣ ከሥልጣን ወደ አደራ፣ ከአደራ ወደ ተግባር የሚወስድ የዴሞክራሲ ሂደት ነው። ከእያንዳንዱ ድምፅ ጀርባ አንድ ዜጋ አለ፤ ከእያንዳንዱ ዜጋ ጀርባ አንድ ቤተሰብ፣ አንድ ሕልም፣ አንድ ተስፋ እና አንድ የነገ ርዕይ አለ።
ሕዝቡ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ከ52 ሺህ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ተሰልፎ ድምፁን ሲሰጥ በካርዱ ላይ የሰፈረውን የመረጠውን ፓርቲ የምርጫ ምልክት ሳይሆን ስለ ሀገሩ የሚያስበውን ተስፋ ነው።
ኢትዮጵያውያን መንግሥታቸውን መርጠዋል። አዲሱ መንግሥት ደግሞ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት ነገ በይፋ ሥራውን ይጀምራል።ኢትዮጵያውያን ጓጉተው ሲጠብቁት የነበረው ቀን ደርሷል።ጨበክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ምስረታ ተካሂዷል። በነገው ዕለት ደግሞ ነገ አዲሱ የፓርላማ የሥራ ዘመን መክፈቻና የመንግሥት ምስረታ ይካሄዳል። የዚህ መንግስት ምስረታ ጉዞ የጀመረው ግንቦት 24 በተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው። ሕዝብ ድምፁን ሲሰጥ ሥልጣንን ብቻ አይሰጥም፤ አደራ ይሰጣል። መንግሥት ሲመሠረትም የሚያገኘው የሥልጣን ወንበር ብቻ ሳይሆን የሕዝብ እምነትን የሚሸከም ከባድ ኃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያ በነገው ዕለት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝብ በድምፁ ያሳለፈውን ውሳኔ ወደ መንግሥት ምሥረታ በማሸጋገር አዲስ ምዕራፍ ትጀምራለች። ይህም ኢትዮጵያ በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በተቋማዊ መንገድ የመንግሥትን ሥልጣን የምታሸጋግር ሀገር መሆኗን የምታሳይበት ታሪካዊ ክስተት ነው።
በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግርና የልዩነት አፈታት ሁልጊዜ በሰላማዊ የሀሳብ የበላይነትና በዴሞክራሲያዊ ፉክክር አልተመራም። የኃይል አማራጭ ብዙ ጊዜ ተሞክሯል። ይህም ብዙ ችግር ወልዷል። ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን አባክኗል። ሀገርን በአብዮት ፍዳ ደፍቋታል።ዛሬ ግን በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ መሠረት ላይ የዴሞክራሲ ድልድይ ፈጥሮ የተካሄደው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይህን የቆየ የፖለቲካ መጥፎ ልማድ በመሻገር ሀገሪቱ ወደ ሰለጠነ የሀሳብ ፖለቲካና ወደ ዘመናዊ የመንግሥት ግንባታ እየተሻገረች መሆኗን አሳይቷል።
የዚህ ለውጥ ትልቁ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተሳትፈዋል። ምርጫው እንዳይሳካ በጠላት የተሞከሩ ከባድ ፈተናዎችን አልፈው፣ ማስፈራሪያና እንግልትን በጽናት ተሻግረው ከማለዳ እስከ እኩለ ሌሊት ተሰልፈው፣ ቁርና ሐሩር ሳይበግራቸው ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ይበጀናል ያሉትን መንግሥት መርጠዋል። ሕዝቡ ለመረጠው መንግሥት የሰጠው ባዶ ካርድ ሳይሆን የሚፈጸም አደራም ነው።
ኢትዮጵያ ነገ የምትጀምረው አዲስ ምእራፍ ከሕዝብ ድምፅ ወደ ሥልጣን፣ ከሥልጣን ወደ አደራ፣ ከአደራ ወደ ተግባር የሚወስድ የዴሞክራሲ ሂደት ነው። ከእያንዳንዱ ድምፅ ጀርባ አንድ ዜጋ አለ፤ ከእያንዳንዱ ዜጋ ጀርባ አንድ ቤተሰብ፣ አንድ ሕልም፣ አንድ ተስፋ እና አንድ የነገ ርዕይ አለ።ሕዝቡ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ከ52 ሺህ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ተሰልፎ ድምፁን ሲሰጥ በካርዱ ላይ የሰፈረውን የመረጠውን ፓርቲ የምርጫ ምልክት ሳይሆን ስለ ሀገሩ የሚያስበውን ተስፋ ነው።
“የትኛው ፖሊሲ የተሻለ ነው? የትኛውን አቅጣጫ እመርጣለሁ? ምን ዓይነት መንግሥት እፈልጋለሁ? ለልጆቼ ምን ዓይነት ኢትዮጵያን አስረክባለሁ?” የሚሉ ጥያቄዎችን አስቦ ነው ድምፅ የሰጠው። በዚህ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩዎች መሳተፋቸውም ይህንን የሕዝብ ምርጫ ለመወሰን ሰፊ የፖለቲካ አማራጭ ፈጥሯል። ስለዚህ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊነት በአንድ ፓርቲ ድል ብቻ የሚጠቃለል አይደለም።
የዴሞክራሲ ሂደቱ ራሱ አሸናፊ ሆኗል። ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ግን በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር ሁልጊዜ በሰላማዊ የሀሳብ ውድድር የተመራ አልነበረም። የኃይል አማራጭ ብዙ ጊዜ በዴሞክራሲ የሚመራ ፖለቲካ ውሳኔን ተክቷል። ሰባተኛው ምርጫ ግን አዲስ መንገድ አሳይቷል። ሥልጣን በኃይል ሳይሆን በሕዝብ ፈቃድና ምርጫ እንደሚመጣ አረጋግጧል። ይህም ለአፍሪካ ቀንድና ለመላው አፍሪካ ምሳሌ ሆኗል።
የአፍሪካ ቀንድ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካዊ ውጥረት፣ በግጭትና በተቋማዊ ድክመት የተፈተነ አካባቢ ነው። በዚህ አካባቢ ምርጫን በሰላም ማካሄድ፣ የሕዝብን ድምፅ ማክበር፣ ውጤትን በተቋማዊ መንገድ ማስተናገድ እና ወደ ሕጋዊ መንግሥት ምሥረታ መሸጋገር እጅግ ትልቅ ትርጉም አለው። የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዚህ ረገድ ለአፍሪካ የሚያስተላልፈው መልዕክት ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ ጠንካራና ገለልተኛ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መፍጠሯን፣ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በነጻነት ይበጀናል ያሉትን መንግሥት መምረጣቸውን፣ በዚህም በኃይል ሥልጣን ለመያዝ የቋመጡ አካላትን ሴራ ማክሸፋቸውን አሳይቷል።
ምርጫው እንዳይሳካ ብዙ የሴራ ድር በጠላትና በባንዳ ተተብትቦ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ “ምርጫው ራሱ የጠላት ኢላማ ነበር” ምክንያቱም የምርጫው መሳካት የሚያሳፍራቸው ብዙ የስሁት መንገደኞች ነበሩ፤ ከግጭት የሚያተርፉ የደም ነጋዴዎችም ነበሩ፣ በኃይል ሥልጣን መናጠቅ የሚመኙ ከንቱ ሕልመኞችም ነበሩ።ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ለፕሮፓጋንዳም ሆነ በጠላት ለተደቀነባቸው አፈሙዝ ሳይበገሩ ድምፅ ሰጥተዋል። ከማለዳ እስከ እኩለ ሌሊት በጽናት ተሰልፈው ሀገርን ለማሻገር ይበጀናል ያሉትን መርጠዋል። በዚህም ጠላት ሲያፍር ኢትዮጵያ ግን አሸንፋለች። ይህ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የፖለቲካ ባህል ላይ ትልቅ ለውጥ ነው።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሌላኛው ድል የሚለካው በውጤቱ ብቻ አይደለም፤ በፖለቲካዊ ተሳትፎ ስፋትና በአካታች ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ባሳረፈው ጉልህ አሻራም ጭምር ነው።በዚህ ምርጫ ከ42 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩዎች በምርጫ ሜዳው ተሳትፈዋል። ይህም የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ለተለያዩ ሐሳቦች፣ አማራጮችና የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች በር የከፈተ መሆኑን ያሳያል።
የዚህ ምርጫ ልዩ ገጽታ ግን በተወዳዳሪዎቹ ቁጥር ብቻ አይወሰንም። ከዚያ በላይ፣ ገዥው ፓርቲ ለተፎካካሪዎች የበለጠ የመወዳደሪያ ዕድል እንዲፈጠር ያደረገው ውሳኔ በራሱ ግዙፍ የፖለቲካ ትርጉም አለው።
ብልፅግና ፓርቲ 15 በመቶ የምክር ቤት ወንበሮችን በሚያስገኙ የምርጫ ክልሎች ላይ እንዳይወዳደር መወሰኑ፣ ለሌሎች ፓርቲዎች የተለየ የፉክክር ሜዳ የፈጠረ እርምጃ ነበር። በሌላ አገላለጽ፣ ገዥው ፓርቲ የራሱን የምርጫ ዕድል በመገደብ ሌሎች የፖለቲካ ድምፆች ወደ ምክር ቤቱ እንዲገቡ ተጨማሪ ቦታ ከፍቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ውሳኔ ሲያብራሩ፣ ዓላማው ብዙ ድምፆች ወደ ፓርላማ እንዲገቡና አካታች ዴሞክራሲ እንዲጠናከር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። በእርግጥም ይህ አንዱ የዴሞክራሲ ጥንካሬ መለኪያ ነው።
ይህ ውሳኔ በምርጫ ወቅት የተወዳዳሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ የተደረገ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገሪቱን ፓርላማ የተለያዩ የሕዝብ ሐሳቦች የሚወከሉበት የበለጠ ውክልና ያለው መድረክ ለማድረግ የተወሰደ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው። ምርጫው የአንድን ፓርቲ ድል ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ ሂደት ብዝሃ ድምፆች እንዲሰሙ ዕድል የፈጠረ ነው።
በዚህ ረገድ የሰባተኛው ምርጫ ዋና ትርጉም ከምርጫ ውጤቱ በላይ ነው። 15 በመቶውን የምርጫ ሜዳ ለሌሎች ተወዳዳሪዎች መተው ደግሞ የአካታችነት መርህን በተግባር ለማሳየት የተወሰደ እርምጃ ሆኗል። ይህ በየትኛውም አፍሪካ ሀገር ያልተደረገ ነው። ብዙ ድምፆች ወደ ፓርላማ ሲገቡ፣ ዴሞክራሲም የበለጠ ይሰፋል። ይህም የሰባተኛው ምርጫ ከውጤቱ በላይ የሚታይበት ሌላኛው ድል ነው። አዲስ የሚመሠረተው መንግሥትም የበርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች የሚሳተፉበት አካታች መንግሥት ነው።
የምርጫ ድል የመንግሥት አደራ ነው። የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት የመመሥረት ሕጋዊ መብት አግኝቷል። ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ በሆነው የ501 የምርጫ ክልሎች ውጤት መሠረትም 438 የፌዴራል ፓርላማ መቀመጫዎችን አሸንፏል። ግን የምርጫ ድል የምክር ቤት ወንበርን በማሸነፍ ቢጀምርም በዚህ አያበቃም። ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር መፈጸም ቅቡልነትን ያጸናል። ይህም ነገ የሚመሠረተው መንግሥት የሚጠብቀው ትልቁ ኃላፊነት ነው። ሕዝቡ መርጧል። አሁን ደግሞ አዲሱ መንግሥት የተጣለበትን አደራ ለመወጣት ነገ በይፋ ሥራውን ይጀምራል።
በመንግሥት ምሥረታው ከመራጩ ወደ ተመራጩ የሚሸጋገረው የአደራ ኪዳንም ይህ ነው። ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ መንግሥት በምርጫ ይመሠረታል። የሚጸናው ግን በሥራ ውጤቱ ነው። የጠንካራ መንግሥትነት መለያውም በሕዝብ የተጣለበትን እምነትና አደራ የሚወጣ፣ ጠንካራ ተቋማትን የገነባ፣ ሕግን ያስከበረ፣ ተፎካካሪ ሐሳቦች የሚደመጡበት እና የሕዝብን ጥያቄ በተጨባጭ ውጤት የሚመልስ መንግሥት ሲሆን ነው።
ስለዚህ ነገ የሚመሠረተው መንግሥት በምርጫ ማኒፌስቶው የገባውን ቃልና በሕዝብ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት የአምሥት ዓመት ጉዞውን በተግባር የሚጀምር መሆን አለበት። ይህ እንደሚሆን ደግሞ ብዙ እርሾዎች አሉት። አሁን የተመረጠው መንግሥት ባለፉት አምሥት ዓመታት ለሕዝብ ቃል ገብቶ ባሳካቸው ድሎች ዳግም ዕድል የተሰጠው ነው። በምግብ ራስን የመቻል ግብን በማሳካት ተረጅነትን አስቀርቷል። ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሕዝብ ቃል በገባው መሠረት አሳክቷል። ሕዝብን ያማረረውን የሌብነትና ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ ዲጂታል የመሶብ አገልግሎትን በመላ ሀገሪቱ አስጀምሯል። የኑሮ ውድነትን ለማቃለልም ምርትና ምርታማነትን በብዙ እጥፍ በማሳደግ እና የተበላሸ የገበያ ሰንሰለትን በማስተካከል ወሳኝ ለውጥ አምጥቷል።
ታላቋን ኢትዮጵያን የሚመጥኑ የክብርና የሉዓላዊነቷ ዘብ የሆኑ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን ገንብቷል። በታላቅ ርዕይ በመመራትም ኢትዮጵያን ከኩስመና የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ወደ ተደማጭና ተፅዕኖ ፈጣሪ ከፍታ አሸጋግሯታል። በቱሪዝም ልማት የኢትዮጵያን መልክ አድምቋል።በከተሞች ኮሪደር ልማት ጉስቁልናን አስወግዶ ከተሞችን ውብ የመዝናኛ፣ የሥራና የምቹ መኖሪያ ማዕከል እያደረገ ይገኛል። ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ከቀደሟት እኩል እንድትራመድ እያደረገ ይገኛል። ማዕድኗን ገልጣ ወደ ሀብት እንድትቀይር በውጤት የታጀበ መንገድን ጀምሯል። በኢንዱስትሪ ረገድም ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ስትራቴጂክ ምርቶች እንድትተካ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
የሕዝብን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስም ባለፉት ዓመታት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቤቶች ከመገንባት ባለፈ በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተጨማሪ ቤቶችን እንደሚገነባ በማብሰር ወደ ሥራ ገብቷል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከኖረችበት ውስብስብ የመከራ አዙሪት ተላቃ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲኖራት ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የገባውን ቃል በተግባር ፈጽሟል። አራት ዓመት ተኩል የፈጀ ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ በወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ኢትዮጵያውያን መግባባት ላይ እንዲደርሱ በማድረግ አዲስ ታሪክ ጽፏል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ሰላምና ዕድገቷን የሚመኙትም ሆኑ የማይመኙትን የምታጓጓ ሀገር እንድትሆን አስችሏል።
ይህ ጉዞ በአዲሱ መንግሥት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ሰላምን ማጽናት፣ ሕግን ማስከበር፣ ለሌብነት የማይመች አሠራርን ማጠናከር፣ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት፣ የኑሮ ውድነትን መግራት፣ የሕዝብን ኑሮ በተጨባጭ መለወጥ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ መሻቶች ማሳካትና ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አካታችነትን ያረጋገጠችና ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን ያረጋገጠች የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገርን መገንባት ለአዲሱ መንግሥት ከሕዝብ የተሰጡ አደራዎች ናቸው።
መንግሥት አደራውን እንዲወጣ ደግሞ የሕዝብ፣ የግሉ ዘርፍ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ መገናኛ ብዙኃንና የእያንዳንዱ ተቋም የተደመረ ትጋት ወሳኝ ነው። ይህ ከተሳካ፣ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ባህል ብቻ ሳይሆን በሕጋዊ የሥልጣን መሠረት፣ የሕዝብን አደራ በመወጣት፣ በአካታች መንግሥትና በልማት ድል የአፍሪካ ሞዴል መሆኗን በተግባር ታረጋግጣለች።