ቀጥታ፡

በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የምርት ትስስር በመፍጠር የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የምርት ትስስር በመፍጠር የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ ገለጹ፡፡ 

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ በመሰነቅ ብልፅግናዋን ለሚያረጋግጡ ዘርፎች ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

ከእነዚህ የልማት አእማዶች መካከል የኢንዱስትሪ እና የማምረቻው ዘርፍ የሚገኙበት ሲሆን የዘርፉን ውጤታማነት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ የፖሊሲና የስትራቴጂ ማሻሻያዎች በማድረግ ጭምር እየተጋች ትገኛለች። 


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል በጥሬ ዕቃነት ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ እሴት እንዲጨመርባቸው መደረጉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት እድል እየፈጠረ ነው።

ይህም የውጭ ምንዛሬን ወጪን ከመቀነስ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የተቀነባበሩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግና የንግድ ሚዛንን ለማስተካከል እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ 700 የሚጠጉ አነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር የምርት ትስስር መፈጠሩን ጠቁመው ይህም ለአርሶ አደሮች የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

ፓርኮቹ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስፋፋት በአካባቢዎቹ የሚገኙ ማህበረሰቦች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻልም አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም አብራርተዋል።

መንግሥት በአጠቃላይ 17 የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማቋቋም ማቀዱን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ተቋቁመው ምርት እያመረቱ ይገኛሉ ብለዋል።

የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን በተለያዩ ክልሎች ማስፋፋት በየአካባቢዎቹ ተመጣጣኝ የልማት እና የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጨምረው ገልጸዋል።


 

የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰናይት መብሬ በበኩላቸው፣ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንቨስትመንት ሳቢነትን በማሳደግ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ፍሰትንና የሥራ ዕድልንና የተኪ ምርትን ለማሳደግ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በነቀምቴ የሚገነባው የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ወደ ማጠናቀቂያ ደረጃ መድረሱንና ከተለያዩ ሀገራት ኢንቨስተሮችን በማምጣት የንግድ ትስስርን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና የፓርኮቹን የምርት አቅም ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም