ቀጥታ፡

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት አገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱን ይበልጥ ማስቀጠል ይጠበቅበታል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ አገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱን ይበልጥ ማስቀጠል ይጠበቅበታል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ። 

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ በመሰነቅ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚያስችሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምራ በመጨረስ በተግባር አሳይታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት በቀጣይ የሚገነቡ የ30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ጉባ ላይ ማብሰራቸው የሚታወስ ነው።

በወቅቱ ከተበሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ የጋዝ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ፣ 2ኛውን የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተመዘገበ የሚገኘውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠልና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት ማጠናቀቅ የአዲሱ መንግሥት ዋነኛ ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ምሁራን አስገንዝበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት እና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ ለማድረግ በመንግሥት የተወሰዱ የፖሊሲና የሪፎርም ለውጦች  ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። 

በተጨማሪም በሀገሪቷ በልዩ ልዩ ብዝሃ ኢኮኖሚ መስኮች ላይ እየተከናወኑ የሚገኙት መሰረተ ልማቶች፤ ሜጋ ፕሮጀክቶች  የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷ  የተረጋገጠባት ሀገርን መገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ለአብነትም የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ለማሻሻል፣ ትራንስፖርትን ለማዘመን፣ የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን ላይ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለሀገር እድገት የሚኖራቸው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴዎችም ለኢኮኖሚው የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ማየትም ተገቢ መሆኑን አክለዋል።

ፕሮፌሰር ጣሰው አያይዘው፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ የተከናወኑ የሪፎርም ማሻሻያ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲነቃቃ ያደረገ ለኢንቨስተሮች ምቹ ምህዳርን የፈጠረ ነው ብለዋል።

የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶ/ር ብርሃኑ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የማጠናቀቅ አቅም መገንባቷና መጨረስ ላይ ትኩረት ማድረጓ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያፋጥን ገልጸዋል። 

እነዚህ ግዙፍ የልማት ስራዎች ጠንካራ አገራዊ ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ አገሪቷ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችሉ ሀብቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለአብነት ያህል፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ምርታማነትን ከመጨመሩ ባሻገር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ በመሆኑ፣ ፕሮጀክቱ ለአገሪቷ ኢኮኖሚ ያለውን ላቅ ያለ አስተዋጽኦ በግልጽ እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

የማዳበሪያ ፋብሪካና የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ መሸጋገራቸው የግብርናና የትራንስፖርት ዘርፎችን በማዘመን የአገሪቱን ከፍታ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምሁራኑ እንደሚገልጹት፤ በአገሪቷ የተጀመሩትን ሜጋ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና ለብዝሃ ዘርፎች ትስስር ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ይህ ታላቅ አገራዊ ስኬት እውን ይሆን ዘንድ አዲሱ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ከመወጣቱም በላይ ምሁራን፣ ማኅበረሰቡና ባለድርሻ አካላት በእውቀትና በሀብት ድጋፍ አድርገው ለልማቱ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

እነዚህ የተቀናጁ ሀገራዊ ጥረቶችና የልማት ፕሮጀክቶች አገሪቱን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ከፍታና ብልፅግና የሚያሸጋግሩ አዎንታዊ እርምጃዎች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም