አዲስ የመንግስት ምስረታ - ለላቀ የሀገር ከፍታ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የመንግስት ምስረታ - ለላቀ የሀገር ከፍታ
መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ አዲስ የመንግስት ምስረታ - ለላቀ የሀገር ከፍታ
ታላቅ ሀገር፣ ታላቅ ሕዝብ እና ትልቅ ርዕይ
ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ በተለያዩ የለውጥ ምዕራፎች ውስጥ አልፋለች። የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የዲፕሎማሲ ጉዞም በየዘመኑ ከነበሩ ሁኔታዎች ጋር ተለዋውጧል። ዛሬም ሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ወደ ተሻለ ውጤት ለማሸጋገር፣ በብዝሃ ፖለቲካ ውስጥ ብዝሃ ሃሳቦችን ለማስተናገድ እና በዓለም መድረክ ብሔራዊ ጥቅሟን በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ትገኛለች።
በጨፌ ኦሮሚያ የጀመረው የክልሎች የመንግሥት ምሥረታ በትናንትናው ዕለት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታ ተጠናቋል። የሶማሌ፣ የአማራ፣ የሐረሪ፣ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የሲዳማ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችና የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔዎቻቸውን በማዋቀር ወደ ሥራ ገብተዋል። በዚህም አዲሱ የመንግሥት ምሥረታ ሂደት በክልል ደረጃ ወደ ተግባራዊ ሥራ ተሸጋግሯል ማለት ይቻላል።
የመንግሥት ምሥረታ በራሱ መጨረሻ ግብ ሳይሆን የተሰጠን የሕዝብ ኃላፊነት ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀየርበት የሥራ መነሻና ሃላፊነት ነው። በመሆኑም አዲስ የተዋቀረው የመንግሥት አስተዳደር የሕዝቡን የልማት፣ የሰላም፣ የፍትሕና የተሻለ አገልግሎት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም በመሰነቅ ሊሆን ይገባል።
የክልል ምክር ቤቶች የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን የሚወክሉ አባላትን በማካተታቸው የሕዝብ ጉዳዮች በተለያዩ እይታዎች እንዲመረመሩ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። የክልሎች የመንግሥታት ምሥረታ በስኬት ተጠናቆ በነገው እለት ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ምሥረታ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል።
በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የሚከፈተው አዲሱ የፓርላማ ዘመን፣ የአፈ ጉባኤና የምክትል አፈ ጉባኤ ምርጫ ማካሄድ የመጀመሪያው ስራ ይሆናል። በመቀጠልም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ የምክር ቤት ወንበር ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዕጩ በማቅረብ በምክር ቤቱ የሚያጸድቅ ይሆናል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ የካቢኔ አባላት ሹመትም በተመሳሳይ በምክር ቤቱ አጽድቆ ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ።
አዲሱ የመንግሥት ቀጣይ የቤት ስራ የተቋማት ምሥረታ ብቻ ሳይሆን የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ማስቀጠል ነው። ባለፉት ዓመታት በግብርና፣ በመስኖ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም፣ በኃይል ልማት እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የተመዘገቡ እመርታዎችን በላቀ መልኩ ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
የመስኖ ስንዴ ምርትን በማስፋፋት፣ የሌማት ትሩፋትን በማጠናከር፣ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ምርትን በማስፋፋት፣ የማዕድን ሀብትን በአግባቡ በማልማት፣ የዲጂታል ሽግግርን በማፋጠን እና የቱሪዝም ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት በመቀየር ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት መትጋት ይጠበቅበታል።
እነዚህ ሥራዎች በተቀናጀ መንገድ ከተመሩ የኢትዮጵያን ምርታማነት ከማሳደግ ባሻገር የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን፣ የሀገር ውስጥ አቅምንና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ ትልቅ ትርጉም ይኖራቸዋል።
የሀገር ግንባታ ሂደት የአንድ ጊዜ ስራ ብቻ ባለመሆኑ በተደመረ አቅም በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ማላቅ እና የተቋማት ግንባታን አጠናክሮ መቀጠልንም ይጠይቃል። የኢትዮጵያ የልማት አቅም ከውስጥ ጥንካሬም ባሻገር ቀጣናዊና አህጉራዊ የልማት ትስስርንና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት የሚያደርግ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጎላ መሄድ የሚችለው በተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም፣ በአካባቢያዊና አህጉራዊ ትብብር፣ በጠንካራ የተቋማት ግንባታና በገቢር ነበብ የውጭ ፖሊሲዋ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጎረቤት አገራትን የሚያስቀድም፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ የልማት ትስስርንና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት ያደረገ እንዲሁም የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ሰንቆ የያዘ መሆኑም ይታወቃል። የቀይ ባሕር እና የቀጣናው ጂኦፖለቲካ መሰረት ያደረገ፤ በሁለቱ ውሃዎች ዙሪያ (አባይ እና ቀይ ባህር) የኢትዮጵያ ህልውና መሰረቶች መሆናቸውን በማስረገጥም ነው። በመሆኑም አዲስ የሚመሰረተው የመደመር መንግስት እነዚህን ሀገራዊና አህጉራዊ ተልእኮዎች ለመወጣት የሚያስችል አቅም በማካበት ይሆናል።
ኢትዮጵያ- ታላቅ ሀገር፣ ታላቅ ሕዝብ እና ትልቅ ርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር ለማስቀጠል በቀጣይ በዙ ስራዎችን ይጠይቃል። በሚቀጥሉት አምስት አመታት በሕዝብ ኑሮ ማሻሻል፣ በልማት ሰራዎች ቀጣይነት፣ በሰላምና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የሚተካ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል። አዲሱ የመንግስት አመራርም ፅኑ አቋም በመያዝ ለዚሁ ስኬት የተዘጋጀ መሆን ይጠበቅበታል።
ከባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን በመቀመር፣ የነበሩ ችግሮችን በማረም፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ እና አዳዲስ ዕድሎችን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ማድረስ ይገባል። በዚህ ረገድ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ብዙ ስራዎች የሚጠብቁት ይሆናል።
የአዲሱ የመንግሥት ምሥረታ የሀገርን የልማት ጉዞ ወደ ተሻለ ምእራፍ የማሸጋገር አላማ የሰነቀ እና በተግባርም የሚችል መሆኑን መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። በግብርና ልማት ምርታማነትን በማሳደግ ከድህነትና ከተረጅነት በመውጣት የሀገርን ክብር ማስጠበቅ እንዲሁም አሰባሳቢና የጋራ ትርክት በመገንባት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባትን ዋነኛ ትኩረቱም ሊሆን ይገባል።