ቀጥታ፡

የሉዓላዊነት መከታ፣የቀጣናው መረጋጋት ዋስትና-የሀገር መከላከያ ሰራዊት

ኢትዮጵያ የበርካታ መስዋዕትነቶች ድምር ውጤት ናት። በረጅም ዘመን ታሪኳ ዜጎቿ ለነጻነቷ፣ ለክብሯና ለሉዓላዊነቷ ከባድ ዋጋ ከፍለውላታል።ምንም እንኳን በየዘመኑ ጠላቶቿ ቢበዙና ባንዳዎች ቢበረክቱም፤በጀግኖች አርበኞችና በጽኑ ልጆቿ ተጋድሎ ምድረ-ቀደምቷ ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስክብራ ዛሬ ላይ ቆማለች።

በየጊዜውና በየታሪክ ምዕራፉ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ የራሷንም ሆነ የቀጣናውን ደህንነት ለማስጠበቅ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል። አይነቱንና መልኩን እየቀያየረ የሚመጣውን የዘመኑን ጥቃትና ትንኮሳ በመከላከልና ሀገራዊ ልዕልናን በማስጠበቅ በኩል ደግሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግንባር ቀደሙን ድርሻ ይይዛል።

ኢትዮጵያ ለዘመናት በነጻነት የኖረችውና ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛች የአፍሪካ ሀገር የተሰኘችው በዘፈቀደ አይደለም። ከሩቅ የመጡ ወራሪዎችን በጀግንነት ድል በማድረጓ፣ ከቅርብ ያንዣበቡ ጠላቶቿንም አሳፍራ በመመለሷ እንጂ።

ለዚህ ደግሞ ከአፍሪካ አልፎ የሰው ልጆች ሁሉ የጀግንነትና የመስዋዕትነት ውጤት የሆነው የጥቁር ህዝቦች መመኪያ ታላቁ ዓድዋ ድል ሕያው ምስክር ነው፤ በዚህም ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ሀገር ሆና ዘልቃለች።

የዘመናዊው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቅኝትና ስሪትም ከቀደምት አባቶች በወረሰው የሀገር ፍቅርና የጀግንነት እሴት ላይ የተመሠረተ ነው። ሠራዊቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ዋስትና፣ የዳር ድንበር ዘብ እና የነጻነት መከታ ሆኖ ዘልቋል።

ከሕዝብ አብራክ የተወለደና ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ በመሆኑ ሕዝባዊ ባህሪው የታወቀ ነው። ከግላዊ ጥቅም ይልቅ የሀገርን ህልውና ማስቀደሙ የብሔራዊ ጥቅሞች ዋና ማስከበሪያ ያደርገዋል። የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበርና የሕዝብን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ለሕይወቱ የማይሳሳ በመሆኑም ‘የሉዓላዊነት ምሽግም ነው።

በእርግጥ የኢትዮጵያ ሠራዊት ገድል ከሀገር ወሰን የተሻገረና ከአህጉርም የዘለለ ነው። በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያሳየው አኩሪ ገድል ስሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ በወርቅ ቀለም አስጽፎታል። ለዚህም የኮሪያ ባሕረ-ሰላጤ፣ የኮንጎና የላይበሪያ ጫካዎች፣ የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን ምድረ-በዳዎች እንዲሁም የሩዋንዳ ኮረብታዎች ሕያው ምስክሮች ናቸው።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ከተካሄዱት ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ሥራዎች በኋላ ተቋማዊ አቅሙን በማጎልበት በሙሉ ቁመና ላይ ይገኛል። ተቋማዊ አደረጃጀቱ ዘመናዊ፣ አስተሳሰቡ ሀገራዊ፣ ዝግጁነቱ ደግሞ አስተማማኝ እንዲሆን ተደርጓል። ሠራዊቱ በስነ-ልቦና፣ በስልጠና እና በውጊያ መሠረተ ልማት ብቃቱን በማላቅ የማይደፈር አቅም ገንብቷል።

በአስቸጋሪ መልክዓ-ምድር ወጥቶ ወርዶ ሀገርን የሚጠብቅ፣ ቁርና ንዳድ የማይበግረው የምድር ኃይል ከመገንባቱም በላይ፤ በመካናይዝድ አቅሙ የላቀ፣ በሳይበር እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የረቀቀ የሀገር ዋስትና ሆኗል።

ትናንትም ሆነ ዛሬ የኢትዮጵያ ሰማይ ዘብ የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በበኩሉ፣ በላቁ የጦር ጄቶች፣ በተዋጊ ሄሊኮፕተሮችና በድሮኖች ተደራጅቶ የአየር ክልሉን በአስተማማኝ ሁኔታ በማስከበር ላይ ይገኛል።

ከድህረ-ለውጥ የሪፎርም ፍሬዎች አንዱ የሆነውን የባሕር ኃይል ዳግም መዋቀር ደግሞ ለቀጣናው ሰላምና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

በታሪኳ መልከ-ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፈችውን ሀገር ጠብቆ ለሉዓላዊነቷ፣ ለሰላሟና ለልማቷ ዋስትና የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ዛሬም በመስዋዕትነቱ ሀገርን እያጸና ያለ የትውልድ ባለአደራ ነው።

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ህዝብ #ታላቅ_ርዕይ

 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም