ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን- የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን- የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች
ሰመራ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚያጠናክሩ በአፋር የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የአፋር ክልል ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት፣ 1ኛ መስራች ጉባዔውን አጠናቋል።
ምክር ቤቱ በመስራች ጉባዔው የክልሉን ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈጉባዔ እንዲሁም ርዕሰ መስተዳድር ሰይሟል።
በምክር ቤቱ ቀርበው በድጋሜ በተሾሙት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ አቅራቢነት የክልሉ አስፈፃሚ አካላት ሹመትንም ማፅደቁ ይታወሳል።
በዚህ ዙሪያ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸውን የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከአዲሱ መንግስት ጋር በንቃት ይሳተፋሉ።
ከከተማ ነዋሪዎቹ መካከል አቶ መአድ አህመድ እንደተናገሩት በከተማዋ ልማቱን በማጠናከር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለተቀየሱ ተግባራት የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።
አዲስ የተመሰረተው መንግስት የተጀመረውን ልማት በማጠናከር እና የኑሮ ውድነትን መቀነስ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ኑሩ ደበሌ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት ያከናወናቸው ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው።
አዲስ የተመሰረተው መንግስትም ይህን በማስቀጠል የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይበልጥ መስራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።
እሳቸውም የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚያጠናክሩ አስረድተዋል።
አዲሱ መንግስት ወጣቶችን ማዕከል ያደረገና አሳታፊ የልማት ስራዎችን ማጠናከር ይገባዋል ያሉት ደግሞ አቶ አህመድ ሙክታር ናቸው።
በቀጣይ የተጀመሩ ተግባራትን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት አጋርነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል ።