በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ውስጥ የዜጎች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ውስጥ የዜጎች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ዜጎች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ውስጥ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህልቁ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በሁሉም መስክ ትርጉም ያለው ውጤት እያስገኘ ነው፡፡
ከሪፎርሙ ትሩፋት መካከል የካፒታል ገበያ መቋቋሙና ዜጎችም በፋይናንስ ዘርፉ ላይ በንቃት እንዲሳተፉና ተጠቃሚነታቸውም እንዲረጋገጥ የተወሰደው እርምጃ ተጠቃሽ ነው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህልቁ፤ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን መቋቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ለማቋቋም በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው ባለስልጣኑ ከተቋቋመ ወዲህ ህጎች እና አሰራሮችን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ገበያው ጠንካራ፣ ተዓማኒ እና አቅም ያለው እንዲሆን በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው በዚህም ጠንካራ ተቋም ሆኖ መቋቋሙን አንስተዋል።
ግልጽ፣ ተገማች እና እምነት የሚጣልባቸው የህግ ማዕቀፎችን ማስተዋወቁን እና ከሁሉ በላይ ባለፉት ሁለት አመታት የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ መስራት እንደሚችል ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ።
በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የተመዘገቡ ኩባንያዎች ቁጥር 26 መድረሱን ጠቁመው ከነዚህም ሰባቱ በሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በወረቀት ተመዝግበው የነበሩ 187 ሺህ የሚሆኑ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ወደ ማእከላዊ ግምጃ ቤት መዞራቸውን ጠቁመዋል።
38 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችም የኢንቨስትመንት አካውንት መክፈታቸውንና አብዛኞቹ በንቃት እየተገበያዩ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ዜጎች በገበያው ላይ ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ በቀን ከ50 እና 60 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
በህብረተሰቡ ዘንድ በገበያው ላይ ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት መጨመር ትልቁ ስኬት መሆኑንም አመላክተዋል።
ወደ ገበያው የሚቀላቀሉ ተዋንያን ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት ጠንካራ ፍተሻ እንደሚደረግ ጠቁመው ማንኛውም የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ እና የሙዓለ ንዋይ አውጪ ወደ ስራ ከገባ በኋላም አሰራሩ ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ለዚህም "Market Survilance" የሚባል በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል።
በአዋጁ በገበያው ውስጥ የተከለከሉ ተግባራት ሊያስከትሉት የሚችለውን አስተዳደራዊ እና የወንጀል ቅጣት ላይ ግንዛቤ መፈጠሩንና እስካሁንም በጥሩ ሁኔታ ግብይቱ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።