የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀና አብሮነትን ባጠናከረ መልኩ ተከብሯል - ኢዜአ አማርኛ
የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀና አብሮነትን ባጠናከረ መልኩ ተከብሯል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀና አብሮነትን ባጠናከረ መልኩ መከበሩን የቱለማ አባ ገዳ ቱለማ ጌቱ ተሊላ ገለጹ፡፡
አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ የዘንድሮው ኢሬቻ ህብረትን በሚያጠናክር መልኩ በፍቅር እና በአንድነት ተከብሯል ብለዋል።
በዓሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የታደሙበት በዓል እንደነበር ጠቅሰው ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገራት የመጡ በርካታ ታዳሚዎች በጋራ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ስኬታማ በሆነ መንገድ መከበሩንም አንስተዋል።
አባ ገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው፤ የበዓሉ ታዳሚዎች በባህል አልባሳት ተውበው አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል ብለዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ፤ የዘንድሮው የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል ልዩ ገጽታ የመሠረተ-ልማት ግንባታው መሻሻል መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ወደ መልካው የሚያደርሰው መንገድ አንድ ብቻ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ አስፈላጊ የመሠረተ-ልማት አቅርቦቶች ተሟልተው ህዝቡ ያለ ምንም እንግልት አክብሮ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።
ከንቲባው አያይዘውም የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።