ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለመስኖ እና ለውሃ አቅርቦት አገልግሎት የሚውሉ ግድቦችን የመገንባት መብቷን እየተጠቀመች ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከሉዓላዊ መብቷ፣ ከውሃ ፖሊሲዋ እና ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለመስኖ እና ለውሃ አቅርቦት የሚውል ግድብ በመገጭ ወንዝ ላይ እያጠናቀቀች መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የግብፅ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት የማያደርሱ ግድቦችን ለመገንባት እነርሱን ፈቃድ መጠየቅ እንዳለባት ሲገልጹ እንደሚስተዋሉ አውስተው፤ ይህንን ሲናገሩ መስማት የሚያሳፍር ነው ብለዋል፡፡ 

ባለስልጣናቱ የአስዋንን ግድብ ታሪክ መለስ ብለው መመልከትና ግድቡ ከመገንባቱ በፊት ኢትዮጵያን አማክረው ነበር ወይ ብለው ማሰብ እንዳለባቸው መክረዋል።

ግብፅ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የያዘችው አቋም ጊዜ ያለፈባቸው እና የቅኝ ግዛት ዘመን ላይ የመቸከል አዝማሚያን የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እነርሱ "እኛ የዓባይ ነን፣ ዓባይም የእኛ ነው ይላሉ" ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ኢትዮጵያ ለዓባይ ተፋሰስ የምታደርገውን አስተዋጽኦ ችላ ያለ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ያላገናዘበ ነው ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዋናነት ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የተገነባ መሆኑን ተናግረው፤ መገጭ በግብፅ ላይ ምንም ዓይነት ጎልቶ የሚታይ ጉዳት የማያደርስ የዓባይ ገባር ወንዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመስኖ የመጠቀም መብት አላት ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሀገራዊ እቅዶቿ ቅደም ተከተል መሠረት የውሃ መሰረተ ልማቶችን ማልማቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

የመገጭ ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት ኢትዮጵያ የሉዓላዊ የመልማት መብቷን እየተጠቀመች ለመሆኑ ማሳያ አድርገው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊትና የራሷ መንግስት ያላት የራሷ ሥርዓትና ፖሊሲ የምትከተል ሀገር ናት ያሉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የልማት ተግባራት የማንንም ፈቃድ እንዳማትፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነትን የተመለከተው አቋም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፤ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብና የውሃ የበላይነት በመያዝ በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎት ጊዜው ያለፈበት መሆኑን አመልክተዋል።

በተፋሰሱ ሀገራት በኩል ያሉትን ወንድሞቻችንን ግምት ውስጥ እናስገባለን ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፤ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር አብሮ በማደግና ለእነርሱም በማሰብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አብራርተዋል።  

በኢትዮጵያ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ ለረጅም ዘመናት የቆየ መሆኑን አስታውሰው፤ ግብፅ እኤአ በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ተቃውሞ ስታቀርብ እንደነበር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምላሽ የውሃ ልማት ፍላጎቷን ለማሟላት የውሀ ሀብቷን ማልማቷንና ወደፊት መራመዷን መቀጠል ነው ብለዋል። በተለያዩ ጊዜያት የግብፅ ባለስልጣናት የሚናገሩት ንግግር ካይሮ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት የምትከተለውን ፖሊሲ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ጥሬ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ መሠረት የውሃ ሀብቷን የማልማት ሉዓላዊ መብት እንዳላት ገልጸዋል።

የአስዋን ታላቅ ግድብ ሲገነቡ ኢትዮጵያን ሳያማክሩና ሳያስፈቅዱ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ እኤአ 1959ኙ የዓባይ ውሃ ስምምነት ኢትዮጵያን አግልሎ በግብፅና በሱዳን መካከል መደረጉን ተናግረዋል።ይህም የውሃ ክፍፍል በሁለቱ ሀገራት ብቻ እንዲወሰን አድርጓል።

በዚህም ኢትዮጵያ የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ያገለሉ አሰራሮችን የተቃወመች ሲሆን፤ በወንዙ ላይ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም የማግኘት መብቷን አጽንኦት ሰጥታ ስትገልጽ ቆይታለች።

አሁን ላይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አጠናቃ እንደ መገጭና ሌሎች ግድቦችን እየገነባች ትገኛለች፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም