ቀጥታ፡

የልማት እቅዶችን ለመፈፀምና ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል - የስራ ሃላፊዎች

ሀዋሳ ፤መስከረም 24/2019(ኢዜአ) :- የተያዙ የልማት እቅዶችን ለመፈፀምና ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት በገባነው ቃል መሰረት ሃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የሲዳማ ክልል የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ገለጹ።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው መስራች ጉባኤ ርእሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችን ሹመት በማጽደቅ በይፋ ስራ የተጀመረ መሆኑ ይታወቃል።

በርእሰ መስተዳደሩ የቀረቡ አስፈፃሚዎችም በምክር ቤቱ ሹመታቸው ፀድቆ ቃለ ማሃላ ፈፅመው የመንግስትና የህዝብ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከተሿሚዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አበራ አርጎ (ዶ/ር)፤ በተለይም የትውልድ ግንባታ መሰረት በሆነው የትምህርት ሴክተር ህዝብን ማገልገልና ሃላፊነትን መወጣት ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።

በትምህርት ዘርፉ ባለፉት አምስት አመታት የመጡ ለውጦችና የተመዘገቡ ስኬቶች የሚደነቁ መሆኑን አንስተው በቀጣይ ህዝብንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በተደመረ አቅም ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የተሰጠው ትኩረትና የመጣው ውጤት መልካም መሆኑን የገለጹት ሃላፊው የተሻለ ውጤት ለማምጣት በቀጣይ ብዙ ስራ ይጠብቀናል ብለዋል።

በክልሉ የተያዙ የልማት እቅዶችን ለመፈፀምና ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት በገባነው ቃል መሰረት በተደመረ አቅም ሃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ አዳዲሶችን በመገንባትና የመምህራንን አቅም በማጎልበት ጭምር የዘርፉን እድገትና ማንሰራራት ለማስቀጠል እንሰራለን ብለዋል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወሰንየለህ ስምኦን፤ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የገዥ ትርክት ግንባታ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር ለህብረ ብሄራዊ አንድነትና የሀገር ግንባታ በልዩ ትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ትልቅ ሃላፊነት ያለበት መሆኑን በማንሳት የክልሉ መንግስት ኮሙንኬሽን በትጋት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በክልሉ የተያዙ የልማት እቅዶችን ለመፈፀምና ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ሃላፊዎቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም