ቀጥታ፡

በዞኑ የሚገኙ የየቱሪዝም መስህቦችን የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

ጭሮ ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን በመለየት የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት አስታወቀ። 

ምዕራብ ሐረርጌ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙና በታሪካዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ሀብቶቻቸው ከሚታወቁ ዞኖች አንዱ ነው። 

አካባቢው በረጅም የደጋ፣ ወይናደጋና ቆላማ የአየር ንብረት የተከፋፈለ በመሆኑ ለተለያዩ የተፈጥሮና የዱር አራዊት ሀብቶች ምቹ ስነ-ምህዳር አለው። 

በዞኑ ከሚገኙ ደኖችና የተፈጥሮ ተራሮች መካከል የጨርጨር ተራሮች ሰንሰለትና የጭላሞ ደን የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክና ከሐረር ዝሆን መጠለያ ጋር የሚያያዙት ቆላማ ቦታዎች ደግሞ የበርካታ አጥቢ እንስሳትና አእዋፋት መኖሪያ ናቸው።

በሌላ በኩል፣ ዞኑ በርካታ ሰው ሰራሽና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን አቅፎ ይዟል። 


 

በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ሴክተሩን በመደገፍና የአካባቢ ቅርሶችን በማልማት የገቢና የሥራ ዕድል ምንጭ ለማድረግ ለተያዘው ሀገራዊ አቅጣጫ ምላሽ ለመስጠት፣ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ቅርሶቹን የመለየት፣ በካርታ የመደገፍ፣ ይዞታቸውን የማረጋገጥና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች የማስተዋወቅ የተቀናጀ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

በዞኑ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ቡድን መሪ አቶ ሳኖ አደም ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ የቱሪዝም አቅምን በማሳደግ የጎብኚዎችን ቁጥር እንዲጨምር እና ከዘርፉ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቷል።

በዞኑ 15 ወረዳዎች የሚገኙ ከ50 በላይ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በመለየት የማልማት እና የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ  መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ በቅርስነት ከተለዩት መካከል  የተለያዩ ዕድሜ ጠገብ ዋሻዎች ፣ ፓርኮች፣ ሃይማኖታዊ ቅርሶች እና የጨርጨር ሀይቅ እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

በዞኑ ዳሮ ለቡ ወረዳ የሚገኘውና ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳለው የሚገመተውን የአይናጌ ዋሻን ለቱሪዝም ልማቱ ለማዋል በተለያዩ ዘዴዎች ከማስተዋወቅ በተጨማሪ  አካባቢውን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የዳሮ ለቡ ወረዳ  አስተዳደር በዚህ ዓመት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመያዝ  የመንገድ መሰረተ ልማት የማሻሻል ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ከአይናጌ ዋሻ በተጨማሪ የጨርጨር ሀይቅ ዳርቻን የቱሪዝምና የመዝናኛ መዳረሻ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። 

በሀይቁ ዙሪያ የመዝናኛና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስፋፋት የዞኑን 15ቱንም ወረዳዎች በማሳተፍ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ  በጀት አካባቢውን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ለማከናወን መታቀዱን  አንስተዋል።

በሀይቁ ላይ  ከመሰረተ ልማት ግንባታ በተጨማሪ  የመጓጓዣ አገልግሎትም እየተሻሻለ መሆኑን የገለፁት ቡድን መሪው፤ የቦኬ፣ ኦዳ ቡልቱምና ሀብሮ ወረዳዎች የሀይቅ ላይ መጓጓዣ ጀልባዎችን ገዝተው ወደ አገልግሎት ማስገባታቸውን  አስረድተዋል።


 

በዞኑ ከሶስት ዓመታት ወዲህ የተመሰረቱት ሁለት ፓርኮችን ጨምሮ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ጥንታዊ ቤተ እምነቶችም ለቱሪዝም መስህብነት ትልቅ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የኡላ ቁኒ መስጊድና የአሰቦት ገዳም ዋነኞቹ መሆናቸውንና  በስፋት ለማስተዋወቅ፣ ለጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግና የቱሪዝም ሀብትነታቸውን ለማጎልበት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የቦኬ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ  መሐመድ ዘይን ጀማል እንዳሉት፣ የወረዳው አስተዳደር በተጠናቀቀው ዓመት  ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የጨርጨር ሐይቅ አካባቢን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የመንገድ መሰረተ ልማት የማሻሻል ስራ አከናውኗል።

ሀይቁ ለበርካታ ዓመታት ደርቆ  በአረንጓዴ አሻራ ስራ ዳግም ነፍስ የዘራ በመሆኑ በአካባቢው የተፈጥሮ ጥበቃ ስራውን በማጠናከር እንክብካቤ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም