ቀጥታ፡

በክልሉ እየተመዘገበ የሚገኘው ተጨባጭ ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

ሐረር ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል እየተመዘገበ የሚገኘው ተጨባጭ ለውጥ ዘላቂነት እንዲኖረው የምክር ቤት አባላት የሚያደርጉትን የክትትልና ድጋፍ ስራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የሐረር ከተማ  ነዋሪዎች ገለፁ። 

የሐረሪ ክልል  ምክር ቤት ባካሄደው 7ኛ ዙር 1ኛ ዓመት መስራች  ጉባዔው የምክር ቤቱን አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባኤዎችን እንዲሁም የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ሾሟል።

እንዲሁም ምክር ቤቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የቀረበውን የክልሉን መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሹመት አፅድቋል።

ይህን በማስመልከት አስተያየታቸውን የሰጡት የከተማው ነዋሪዎች የምክር ቤት አባላቱ በክልሉ እየተመዘገበ የሚገኘውን የለውጥ ስራዎች ለማስቀጠል የሚያስችሉ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ወጣት ደረጀ መስፍን እንዳለው በአገሪቷም ሆነ በክልሉ ከተማና ገጠር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨባጭ የለውጥ ስራዎች ተግባራዊ ተደርገዋል።

መንግስትና ህዝብ በጋራ በመሆን የነዋሪውን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ገልጾ፤ የምክር ቤቱ አባላትም በልማቱ ቀጣይነት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገረው። 


 

አቶ ፈጠነ በጅጋ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በምክር ቤቱ ምስረታ ላይ አዳዲስና ልምድ ያላቸው አመራሮች ወደ አመራርነት መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም በክልሉ የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠል ትልቅ ሃላፊነት መሆኑን ጠቁመው እንደ ህዝብም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ሐረርን ውብና ማራኪ በማድረግ ቱሪስቶች እንዲበራከቱ ማስቻሉት የተናገሩት ደግሞ  ወይዘሮ ቲማጅ ጃሚ ናቸው።

በክልሉ የተጀመሩ ስራዎችን የምክር ቤቱ አባላትና አመራሩ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

አቶ አማረ አበበ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው መንግስት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ እና  ክልሉን የለወጡ በርካታ የልማት ስራዎች አከናውኗል ብለዋል፡፡

በቀጣይም የክልሉ መንግስት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎችን እንደሚያከናውን ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመው ህዝቡም ይህን መደገፍ እንደሚገባው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም