ቀጥታ፡

የኢሬቻ በዓል የህዝቦችን አንድነት፣ አብሮነትና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ታላቅ በዓል ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦የኢሬቻ በዓል የህዝቦችን አንድነት፣ አብሮነትና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ታላቅ በዓል ነው ሲሉ የቢሾፍቱ ሆረ ሀርሰዴ በዓል ታዳሚዎች ገለጹ፡፡ 

የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል በአባገዳዎች የምርቃት ስነ-ስርዓት ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት የኢሬፈና ስነ-ስርዓት በድምቀት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበትና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለምንበት በዓል ነው፡፡


 

የኢሬቻ ሆረ ሀርሰዴ በዓል ታዳሚ ደረጄ ፍቅሩ በሰጠው አስተያየት፤ ህዝቡ ባህልን የሚገልጹ አልባሳትን ለብሶ በዓሉን በጋራ በፍቅርና በአንድነት እያከበረ ይገኛል ብሏል፡፡ 

የኢሬቻ በዓል ማራኪና ውብ በሆነ ሁኔታ ሁሉም በአንድነት የሚያከብረው በዓል መሆኑን ጠቅሶ በዓሉ አብሮነትንና አንድነትን የሚያጎለብት ነው ብሏል፡፡

ቦረና አበራ በበኩሉ፤ በዓሉ ሥርዓቱን ጠብቆ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው ብሏል፡፡ 


 

ኢሬቻ የኢትዮጵያውያን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ በመሆኑ የእርስ በእርስ መስተጋብርን የሚያጎለብት በዓል መሆኑን ተናግረዋል። 

 ኢሬቻ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ሁሉም የሚሳተፍበት፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ በዓል መሆኑን ገልጿል።


 

ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚ ሲፈን ኡርጌሳ በበኩሏ፤ የበዓሉ ባህላዊ እሴቱ ሳይበረዝ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ጠቅሳለች፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም