የክልሉ መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አዲስ የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋቱ አስደስቶናል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አዲስ የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋቱ አስደስቶናል
አዳማ ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ክልል መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን አዲስ የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋቱ እንዳስደሰታቸው የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል አዲስ የተዋቀረው የመንግስት አስተዳደር የሕዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
ክልላዊ መንግሥቱ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ሥርዓትንና ብቁ መንግሥትን የሚመሠርት አዲስ ሪፎርም ወደ ሥራ ካስገባቸው ታሪካዊ ውሳኔዎች መካከል አንዱ የዞኖች መዋቅር ነው።
የክልሉ መንግስት አዳዲስ ዞኖችን በማዋቀር አስተዳዳሪዎችን በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ በመመደብ በሥራ ላይ ባዋለው በአዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት ክልሉ በስድስት ዞኖች እንዲዋቀር ተደርጓል።
በዚህም በክልል ደረጃ ተንጠልጥሎ ቀርቶ የነበረው አገልግሎት በአዲስ መልክ እስከ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ መዋቅር ተዘርግቶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ይህም በአዲስ አዋጅ የተደነገገ ሲሆን፣ በዚህ አዲስ አደረጃጀት በዞን ደረጃ ሕጋዊ ሥልጣንና የሥራ ድርሻ ያላቸው 23 መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥራ የሚገቡ ይሆናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የዘረጋውን አዲስ የአስተዳደር መዋቅር በደስታ ተቀብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ፋይሳ መገርሣ እንደገለጹት አዲስ የተዘረጋው መዋቅር በክልሉ የተጀመረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የሚያስችል ነው።
ክልሉ በ21 ዞኖች ተለጥጦና ተበታትኖ ነበር ያሉት አቶ ፈይሳ፤ አመች የአስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋትና ሀብቱንና የሰው ሃይሉን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም ብቃት ባለው የሰው ሃይል ለመምረት፣ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግና ፈጣን ለውጥ በሁሉም መስክ ለማምጣት የሚያስችል የክልሉን ካፒታልና የሰው ሃይሉን በተቀናጀ መልኩ ወደ ልማት ለማስገባት አጋዥ የሆነ የአስተዳደር መዋቅር ነው ብዬ አምናለው ብለዋል።
በተጨማሪም አሁን የተጀመረውን አገልግሎትን ዲጂታል የማድረግና ብቃት ባለው የሰው ሃይልና አመራር ለመምራት እድል የሚሰጥ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
አዲሱ የዞኖች አደረጃጀት የመንግስት አገልግሎትና አመራሩ ህዝቡን በቅርበት እንዲያገለግሉ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዲሪባ ጫላ ናቸው።
"ስንመኘውና ስንጠብቀው የነበረ የአስተዳደር አደረጃጀት ነው ተግባራዊ የሆነው" ያሉት አቶ ዲሪባ፤ መዋቅሩ አገልግሎቱን ህዝቡ በቅርበት እንዲያገኝ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
በ21 ቦታ ተበታትነው የነበሩ ዞኖችን ጨምቆ በስድስት ዞኖች ማደራጀቱ አመራሩ ህዝቡን በሙሉ አቅም እንዲያገለግልና ፈጣን ልማትና እድገት እንዲመጣ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተለይም ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ፣ የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ፣የተጀመረውን ልማትና እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል የጎላ ሚና ያለው አደረጃጀት መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙሀመድ አብዱልጀሊል በበኩላቸው አዲሱ አደረጃጀት በብዙ ቦታ የተበታተኑ ዞኖችን ወደ ውስን ዞኖች የመለሰ ከመሆኑም ባለፈ ልማቱን የሚያፋጥን ነው ብለዋል።
በፊት በነበረው የተበታተነ አደረጃጀት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥያቄዎችን ወጥነት ባለው መልኩ ለመመለስ አስቸጋሪ ነበር ያሉት አቶ ሙሀመድ፤ አዲሱ አደረጃጀት በተቀናጀ መልኩ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ አዲሱ መዋቅር ብቃትና ስነ ምግባር ባላቸው የሰው ሃይል እንዲመራ መደረጉ ህብረተሰቡ በየጊዜው ለሚያነሳው ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።