ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በልዩነት ውስጥ መግባባት በመፍጠር ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ማሳያ ሆኗል - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በልዩነት ውስጥ መግባባት በመፍጠር ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ማሳየቱን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የምክክር አጀንዳ ነጥቦችና ምክረ ሐሳቦች ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት በይፋ የማስረከብ ሥርዓት አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ  የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ዐበይት ተግባራት አብራርተዋል።

በዚህም የሀገራዊ ምክክር ጥንስስ ሕዝባዊ ፍላጎት እንደነበረው አስታውሰው፤ የለውጡ መንግሥትም ሕዝባዊ ፍላጎትን  በማሰብ በቁርጠኝነት ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ማድረጉን ገልጸዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታም ከሀገር ውስጥ እስከ ተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ተወካዮችን በግልጽ በመለየት ከሐምሌ 8 2018 ዓ.ም ጀምሮ በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ ውጤታማ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱን አስታውሰዋል።

አራት ሺህ የኢትዮጵያውያን ወኪል ተመካካሪዎችም በ10፣ በ50፣ በ250 እና በሥራ ቡድን አማካኝነት ውጤታማ ምክክር በማካሄድ ለሀገራዊ መግባባት መሠረት የጣሉ ምክረ ሐሳቦች ማቅረባቸውን  አንስተዋል።

በዚህም 400 የሚጠጉ ዝርዝር ምክረ ሐሳቦችና 80 የሚጠጉ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያና የሕግ አሠራር ሥርዓት የሚሹ እጅግ መሰረታዊ ምክረ ሐሳቦች መቅረባቸውን አስረድተዋል።

በምክክር ሂደቱም ድጋፍ ላደረጉ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ተቋማት፣ አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ምክረ ሐሳቦችን በመሰነድ ለፌዴራል መንግሥት፣ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታትና የከተማ አስተዳደሮች የምክክር ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በልዩነት ውስጥ መግባባት በመፍጠር፣ የምክክር ባህል በማዳበርና ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ያሳየ ወሳኝ ሁነት መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም ተመካካሪዎች በልዩነት ውስጥ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል ያሳዩበት ታሪካዊ ሂደት እና የጋራ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም