ምክር ቤቱ የሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚ የሚሆኑበትን የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ተግባራዊነቱን በቅርብ ይከታተላል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚ የሚሆኑበትን የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ተግባራዊነቱን በቅርብ ይከታተላል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2019 (ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የሚሆኑበትን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋትና የቅርብ ክትትል በማድረግ ተፈጻሚነታቸውን እንደሚያረጋግጥ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የምክክር አጀንዳ ነጥቦችና ምክረ ሐሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት በይፋ የማስረከብ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ሀገራዊ ምክክር በስኬት በማጠናቀቅ የምክክሩን ምክረ ሐሳብ ያዘለ ሰነድ መዘጋጀቱ አስደሳች ነው።
ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታቸውና ብሔራዊ አንድነታቸው ላይ የሚቃጣውን ማንኛውንም ዓይነት ትንኮሳ በብቃትና በከፍተኛ መስዋዕትነት ሲመክቱና ሲያስከብሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በመላው አፍሪካና በዓለም ደማቅ የዘመናት አኩሪ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን ብለዋል።
ይህ የጀግንነት፣ አርበኝነትና አትንኩኝ ባይነት መንፈስ እንደተጠበቀ ሆኖ በውስጥ ጉዳዮች ተደማምጦና ተመካክሮ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በሀገራዊ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመገንባት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማፋጠን ፈታኝ ሆኖ መቆየቱንም ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት የትርክት መዛባትን፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለማስተካከል መጠነ ሰፊ ርብርብ በማድረግ የሚታይና የሚዳሰስ ውጤት መገኘቱን አስገንዝበዋል።
ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነትና በወሰዱት ቁርጠኛ አቋም አካታችና ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር መካሄድ መቻሉን አብራርተዋል።
ይህንን ርዕይና የመንግሥትን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙን አስታውሰዋል።
በማቋቋሚያ አዋጁም ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አስተያየት ተካቶበት በሥራ ላይ መዋሉን አስገንዝበዋል።
በአዋጁ መሠረትም መስፈርቱን የሚያሟሉ፣ የምክክር ሂደቱን የሚመሩና የሚያስተባብሩ 11 ኮሚሽነሮችን ለመሰየም 632 ዕጩዎች መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ዕጩዎቹን ወደ 75፣ 42 እንዲሁም ወደ 11 ለመውሰድ የትምህርት ዝግጅትንና የሥራ ልምድን ጭምር በማካተት አሳታፊና አካታች ምልመላ በማካሄድ መሾማቸውንና ሂደቱ የነበረውን ግልጽነት አስረድተዋል።
ኮሚሽኑም ተቋሙን በማደራጀት፣ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ የምክክር ሥነ-ዘዴ በመቅረጽ፣ ሀገራዊ ጉባኤ አጀንዳዎችን በማሰባሰብና ተሳታፊዎችን በማስመረጥ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጉባኤው መጀመሩን አስታውሰዋል።
አራት ሺህ የምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎችም በስምንት ዐበይትና ንዑሳን አጀንዳዎች ተከባብረውና ተደማምጠው የሀገርን የውይይትና የፖለቲካ ባህል የሚቀይር መሠረት የጣለ አስደማሚ ምክክር ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያን ወኪል ተመካካሪዎች በአጀንዳዎቹ ዙሪያ ያቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦችም በምክክር ኮሚሽኑ ምክር ቤት በዝርዝር ታይቶና አስተያየት ታክሎበት በሰነድ መልክ ተዘጋጅቶ መረከባቸውን ተናግረዋል።
ሰባተኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሐሳቦቹ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የሚሆኑበትን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋትና ቅርብ ክትትል በማድረግ ተፈጻሚ እንዲሆኑ እንደሚያደርግም አስታውሰዋል።
የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታትና የከተማ አስተዳደሮች ለምክረ ሐሳቦቹ ተግባራዊነት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የክልል መንግሥታትና ከንቲባዎች የተረከቡትን ሰነድ በዝርዝር በማጤን፣ ዕቅድ በማዘጋጀትና ተስማሚ የአሠራር ሥርዓት ተበጅቶለት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የምክክር ጉባኤው ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚነትም አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ለነበራቸው ተቋማትና አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል።