ቀጥታ፡

የፍቅር እና የአብሮነት መገለጫ የሆነውን የኢሬቻ በዓል በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል-የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ፤መስከረም 23/2019 (ኢዜአ)፦የፍቅር እና የአብሮነት መገለጫ የሆነውን የኢሬቻ በዓል በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ እና ታላቅ ርዕይ ያላት ኢትዮጵያ በየዓመቱ በበርካታ የአደባባይ በዓላት ትደምቃለች።

ከነዚህም መካከል የአንድነት እና የፍቅር መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ (ሆረ ፊንፊኔ) በአንድነትና በፍቅር መንፈስ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

ይህ የሰላም እና የምስጋና በዓል ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበትና እሴቶቻቸውን በድምቀት የሚያሳዩበት ልዩ መድረክ ነው።

በዓሉ ዛሬ በአዲስ አበባ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በነገው ዕለት በቢሾፍቱ (ሆረ ሀርሴዲ) በድምቀት መከበሩን ይቀጥላል።

የቢሾፍቱ ከተማም ለክብረ በዓል  የሚመጡ እንግዶችን  በድምቀት እየተቀበለች ትገኛለች።

የከተማዋ ነዋሪዎችም እንግዶችን በታላቅ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ከመቀበል ጀምሮ ለበዓሉ ድምቀት አስፈላጊውን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዋ ትግስት ገዳ በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው  የኢሬቻ በዓል የዋዜማ ድባብ እጅግ ደማቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን በፍቅር፣ በደስታና የአካባቢውን ባህላዊ እሴቶች በጠበቀ አግባብ  በመቀበል ላይ እንገኛለን ብለዋል።


 

ዋቀዮ ጃዳ በበኩላቸው፣ የእንግዶቹ ቆይታ ያማረ እንዲሆን  የባህል አልባሳትን ጨምሮ ከበዓሉ ጋር የሚሄዱ አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና በዓሉንም በጉገጉት እየጠበቅን እንገኛለን ብለዋል። 

ሌላኛዋ የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ ዕጹብ ውብሸት፣ ከተማዋ በበዓሉ የዋዜማ ድባብ መድመቋን ገልጸው እንግዶችን እስከ በዓሉ ማጠናቀቂያው ድረስ ለማስተናገድ  መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊነት እና የማህበራዊ ትስስር ድምቀት ከመሆን ባለፈ ለከተማው ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም