ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከብሔራዊ ምክክሩ የተገኙ የአጀንዳ ነጥቦችንና ምክረ ሐሳቦችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ለፌደራል እና ለክልል መንግሥታት ዛሬ አስረከበ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 23/2019 (ኢዜአ) ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል አመራሮች በተገኙበት በተካሄደ መርሃ ግብር፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከብሔራዊ ምክክሩ የተገኙ የአጀንዳ ነጥቦችንና ምክረ ሐሳቦችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ለፌደራል እና ለክልል መንግሥታት ዛሬ በይፋ አስረክቧል።


 

‎ይህ የሰነድ ርክክብ፤ በምክክርና በሰላማዊ መንገድ የኢትዮጵያን የቆዩ ሀገራዊ ፈተናዎች መፍታት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፤ በመደመር መንግሥት ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ የተበጀለትን የሀገራዊ ምክክር ሂደት አንድ ትልቅ ምዕራፍ እንደሚያበስር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ሂደቱ ለውይይት፣ ለጋራ መግባባት እና ስምምነትን ለመፍጠር የሚያስችል አካታች መድረክ መመስረቱን አመልክቷል።

‎ባለፉት አራት ዓመታትም ይህ ሂደት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ ችሏል።


 

ተሳታፊዎች ባደረጓቸው ሰፊ ምክክሮች እና በተጠናቀቀው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አማካኝነት እይታዎቻቸውን ለማንጸባረቅ፣ ልዩ ልዩ አመለካከቶችን ለመስማት እና የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውን መስኮች ለመለየት ዕድል አግኝተዋል።

የእነዚህ ውጤቶች በይፋ መቅረብ በምክክሩ የተሰበሰቡ እይታዎችንና የውሳኔ ሐሳቦችን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተቀየሰ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም