ቀጥታ፡

መንግሥት በሀገሪቱ ሰላምን ለማጽናት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የድርሻችንን እንወጣለን-የሃይማኖት አባቶች

ባህር ዳር፤ መስከረም 23/ 2019(ኢዜአ)፡- መንግሥት በሀገሪቱ ሰላምን ለማጽናት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የባሕር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሰላምና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከከተማዋ የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት አድርጓል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ ሰብሳቢና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መላከ ብርሃን ፍሥሐ ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የትኛውንም ሃይማኖት በነፃነት ለማራመድ ሰላምን ማጽናት አስፈላጊ ነው። 

ለዚህም መንግስት ፣የሃይማኖት አባቶች፣ ምእመናን እና ማኅበረሰቡ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው ብለዋል። 

ሰላም ከሌለ ሃይማኖትን በነጻነት ማምለክም ሆነ መስበክ የማይቻል በመሆኑ፣ ምእመኑን በማስተማር ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። 

የእስልምና ሃይማኖት አባት የሆኑት ሼህ ኢብራሂም ጸጋዬ በበኩላቸው፣ ማንኛውም የሃይማኖት አባት ከሃይማኖታዊ ተግባራቱ ባሻገር ሰላምን መስበክና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ  አለበት ብለዋል። 

ምእመናን  አምልኳቸውን በተገቢው እንዲያካሂዱ ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ፣ የሃይማኖት ተቋማት ሕዝብን በማስተማር ስራ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ማኅበረ ምእመናን መሪ ቄስ ካሳሁን መንግሥቱ በበኩላቸው፣ የሰላም እጦት ሃይማኖታዊ አስተምህሮን በነጻነት ለማስተላለፍ የሚገድብ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም የሃማኖት ተቋማቱ ሰላምን ከመስበክ ባለፈ፣ ትውልዱ የሀገሩን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ  ኃላፊነት እንዳለበት ሊያስገነዝቡ ይገባል ብለዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን እንደገለጹት፣ የሃይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላም መረጋገጥና ሉዓላዊነት መከበር ከፍተኛ ሚና አላቸው።

ይህንን እድል በመጠቀም መንግሥት ሰላምን ለማጽናት እያደረገ ያለው ጥረት በማገዝ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

 ሰላምን ማጽናት በመላው ሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ፣ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም