የተጀመሩ የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመሩ የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ይጠናከራሉ
ቦንጋ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁና የሕዝቡ ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚሰሩ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን በመሰየም የምስረታ ተከናውኖ በይፋ ስራ የተጀመረ መሆኑ ይታወቃል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የክልሉ ምክር ቤት አባላትም የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አስፈፃሚውን አካል በማገዝ፣ በመደገፍና ቁጥጥር በማድረግ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላቱ በህዝብ የተጣለባቸውን አደራ በቅንነትና በታማኝነት ለመወጣት ስለመዘጋጀታቸውም አረጋግጠዋል።
ከምክር ቤቱ አላት መካከል ኡስታዝ ሸረፈዲን ኑሩ እና አቶ ዳዊት ተሰማ፤ የህዝብ አደራና ሃላፊነት ቀላል አለመሆኑን አንስተው በገቡት ቃል እና በወሰዱት አደራ መሰረት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በጽናት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ መስፍን ጉብላ፤ አዲስ የተመሰረተው መንግስት ብዙ ስራዎች የሚጠብቁት መሆኑን አንስተው ለስኬት እንዲበቃ የሚጠበቅብንን አደራ እንወጣለን ብለዋል።
የክልሉ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ መስከረም 22 ቀን 2019 ዓ.ም በታርጫ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።