ቀጥታ፡

የልብ ሕመምን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ጅማ፤ መስከረም 23/2019 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የልብ ሕመምን ለመቀነስና ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የልብ ቀን  በጅማ ዩኒቨርሲቲ “አንድም የልብ ምት አታምልጠን” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ተከብሯል።


 

የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ፕሬዝዳንትና ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ማኅበራት ሕብረት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እንዳለ ገብሬ በወቅቱ እንዳሉት  በሀገሪቱ አሳሳቢ የሆነውን የልብ ሕመም ለመቀነስና ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው።

ባለፈው ዓመት   በተካሄደው  ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና መርሐ ግብር በ45 ቀናት ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ ዜጎች የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

በተያዘው ዓመት  መርሐ ግብሩን በማስቀጠል ለአንድ  ሺህ ዜጎች ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና ለመስጠት ታቅዶ እስካሁን ለ60 ዜጎች መሰጠቱን ጠቅስዋል።


 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው የልብ ሕመም ችግሮችንና መንስኤዎቻቸውን ለይቶ ለማከምና ለመከላከል የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሥራውን ከአካባቢው ጀምሮ በሌሎችም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የልብ ሕክምና ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ኤልሳዕ ተገኔ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው የሕክምና ማዕከል ከ4 ሺህ በላይ ሕሙማን የልብ ሕክምና ክትትል እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዛሬው ዕለትም የልብ ሕመምን በተመለከተ ተጨማሪ የመከላከል ሥራዎችን ለማከናወን ዩኒቨርስቲው ነፃ የምርመራ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አክለዋል።

የጅማ ከተማ ነዋሪ አቶ ተፈሪ ጋሻው እና ወይዘሮ ትክክል በቀለ በስነ ስርአቱ ላይ ተገኝተው ነፃ የምርመራ አገልግሎት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የቀኑ መከበር የልብ ሕመምን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

የዓለም የልብ ቀን አከባበር ነገ በሚካሄዱ የስፖርት ፌስቲቫሎችና በሌሎች ስነ ስርአቶች ይቀጥላል።

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም