ቀጥታ፡

ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅና የዲፕሎማሲ ልእልናን አጠናክሮ ማስቀጠል አዲስ ከሚመሰረተው መንግስት ይጠበቃል

ጂንካ፤ መስከረም 23/2019(ኢዜአ) :- የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅና የዲፕሎማሲ ልእልናዋን የማስቀጠል ጥረት አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይገባል ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በአንድ ወቅት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ምክንያቱ ሳይታወቅ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ዘልቃለች።

በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረግ ባለፈ በቀይ ባህር በቅርብ እርቀት ላይ ሆና የዳር ተመልካች ሆና ቆይታለች።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ የትውልዱ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል።

በዚህ ረገድ የመንግስት የዲፕሎማሲ ትኩረትና የትውልዱ ፍትሃዊ ጥያቄ በመሆን ላለፉት ጥቂት ዓመታት በስፋት ተሰርቶበታል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ በአንድ ወቅት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ለምን አጣችው የሚለው ጥያቄ እስካሁንም ሊመለስ ያልቻለ በቁጭት የሚነሳ ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ምስክር ከተማ፤ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በታሪክ፣ በመልክአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው የፍትህ ጥያቄ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅና የዲፕሎማሲ ልእልናዋን የማስቀጠል ጥረት አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት ተመራማሪ ግዛቸው መንገሻ (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ የኢትዮጵያ የንግድ ልውውጥ አቅም፣ የምጣኔ ሃብት እድገትና የህዝብ ቁጥር እያደገ በመምጣቱ የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከምጣኔ ሃብትም ባለፈ ከሉአላዊነት፣ ሰላምና ደህንነት ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ በመሆኑ የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ የሆነው የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው ፌዴራሊዝም እና ህገመንግስት መምህር አንዷለም ግርማ፤ በዲፕሎማሲው ረገድ የኢትዮጵያን ተጽእኖ ፈጣሪነትና የብሄራዊ ጥቅሟን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ባለፉት አምስት አመታት መንግስት ያደረጋቸው ጥረቶች የሚደነቁ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ አምስት ዓመታት ሀገሪቷን የሚመራው መንግስት እነዚህን መልካም ጅምሮች አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል። 

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅና የዲፕሎማሲ ልእልናዋን የማስቀጠል ጥረት ዋነኛ ትኩረቱ ሆኖ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም