አስፈጻሚ አካላትን በመከታተልና በመደገፍ ለህዝብ ተጠቃሚነት በትኩረት እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
አስፈጻሚ አካላትን በመከታተልና በመደገፍ ለህዝብ ተጠቃሚነት በትኩረት እንሰራለን
ሀዋሳ፤ መስከረም 23/2019 (ኢዜአ) ፦ የሲዳማ ክልልን የመንግስት አስፈፃሚ አካልን በመቆጣጠር፣ በመከታተልና በመደገፍ ጭምር የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አደራችንን እንወጣለን ሲሉ የምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት የመንግስት ምስረታ ጉባኤውን አካሂዶ በየደረጃው የአስፈፃሚ አካላትን ሹመትም አፅድቆ በይፋ ስራ የጀመረ መሆኑ ይታወቃል።
የክልሉ ምክር ቤት አባላትም የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አስፈፃሚውን አካል በማገዝ፣ በመደገፍና ቁጥጥር በማድረግ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ጠጅቱ ሮማን፤ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙና የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የክልሉን መንግስት አስፈፃሚ አካል በመቆጣጠር፣ በመከታተልና በመደገፍ ጭምር የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አደራችንን እንወጣለን ብለዋል።
"የመረጠኝን ህዝብ በትጋትና በታማኝነት ለማገልገል ቃለ መሀላ ፈጽሚያለሁ" በዚሁ መሰረትም አገለግላለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ሌሎች የምክር ቤት አባላት አቶ መንገሻ ሀናቆ እና ወይዘሮ ትዕግስት ማንኢሳ፤ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ህዝቡን ለማገልገል በገባነው ቃል መሰረት አደራችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።