የሁለት ግድቦች ወግ - ኢዜአ አማርኛ
የሁለት ግድቦች ወግ
ሕዳሴ የቀጣናው የምስራች፤ አስዋን የበደልና ጥፋት ምንጭ
ዓባይ ከኢትዮጵያ ተራሮች ፈልቆ፤ አለት ሰንጥቆ፤ ሸለቆዎችን ተሻግሮ ወደ ምስር ይፈስሳል። ማኅፀኑ ኢትዮጵያ ብትሆንም፣ ጠብታ አብርክቶ ለማታውቀው ግብፅ የሕይወት ምንጭ ሆኖ ኖሯል።ዓባይ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ነው፤ የግብፅን ሐሩር ያረሰረሰ፣ የቀጣናውን የኢነርጂና የኢኮኖሚ ልማት ዕድል የተሸከመ ወንዝ ነው።
አሁን ላይ በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያም ግብፅም እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ግዙፍ ግድቦች አሏቸው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድን እና አስዋን ግድብ።ሁለቱ ግድቦች ግድብነታቸው ሊያመሳስላቸው ቢችልም፣ ታሪካቸው፣ ተፅዕኖአቸውና ለትውልድ የሚያስተላልፉት መልዕክት ግን ለየቅል ነው። በዚህ ወንዝ ላይ ለዓመታት በአልጠግብ ባይነት የተበየነው የግብፅ የውሃ ፖሊሲ፣ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የልማት ፍላጎትን በተደጋጋሚ የሚገድብ አካሄድን ይዞ ቆይቷል። በዚህም መነሻ ያለምንም ማማከርና ያለ ቴክኒካል ውይይት ዓባይን ብቻችንን መቆጣጠር አለብን በሚል እብሪት አስዋን ተገንብቷል።
የአስዋን ግድብ ሥር እንባዎች
አስዋን የግብፅን ታሪክ በእጅጉ የቀየረ፣ የበረሃዋን ምድር በመስኖ ያለመለመ፣ የኃይል ምርቷን እንድታሳድግ ያስቻለ ግዙፍ መሠረተ ልማት ነው። ነገር ግን ከዚህ የልማት ገጽታ ጀርባ ብዙ ዋጋ የተከፈለባቸው የሕይወት ዋጋዎች፣ የተሰደደ ማኅበረሰብና በውሃ ስር የተቀበሩ ታሪካዊ ርስቶች አሉ። ይህ በአስዋን ግንብ ስር በእንባ የተጻፈ የበደል ታሪክ ነው።አስዋን ሲገነባ የኑቢያ ምድር በሰፊው የናስር ሐይቅ ተጥለቅልቋል። ወደ 100 ሺህ የሚደርሱ ኑቢያውያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ኑሯቸው ተናግቷል። ያላቸውን ጥሪት አጥተዋል። ለብዙ ሺህ ዓመታት በትውልድ ተሻግሮ የመጣው ርስታቸውና የኑሮ መሠረታቸው በናስር ሐይቅ ምክንያት ወድሟል።
የኑቢያ ጥንታዊ ቅርሶችም በሐይቁ ስር የመቀበር አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ብዙ ቅርሶች በውሃ ስር ቀርተዋል፤ ሌሎች ደግሞ በዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ዘመቻ ከነበሩበት ተነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረዋል።የአስዋን ሐይቅ በሰው ልጅና በውሃ ሀብት ላይ ያሳረፈው ጫና በዚህም አያበቃም። በበረሃማው ስፍራ የሚገኘው ይህ ግዙፍ ሐይቅ በየዓመቱ እስከ 16 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ በትነት እንዲጠፋ በማድረግ ውሃ ያለ አግባብ እንዲባክን ያደርጋል።
16 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ ማለት ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሚይዘው 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ አንጻር ስንመለከተው፤ አስዋን ግድብ በየ አራት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የሕዳሴ ግድብ የያዘውን ሙሉ ውሃ በትነት ያባክናል እንደ ማለት ነው። ይህ በሰው ልጅ ይውሃ ፍጆታ አንጻር ደግሞ አስዋን ድግብ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለአንድ ዓመት ሙሉ መጠቀም የሚችለውን የቤት ውስጥ የውሃ ፍላጎት በትነት እያባከነ ቀጥሏል።
አስዋን ግድብ የያዘው የናስር ሃይቅ በጣም ሰፊ እና ጥልቀቱ አነስተኛ (Shallow and Wide) በመሆኑ ለፀሐይ ብርሃን የሚጋለጠው አካል ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ የትነት መጠኑ በእጅጉ እንዲጨምር አድርጓል።ይህ በትነት የሚጠፋው የውሃ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት በውሃ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ሁልጊዜም በግብፅ ስሁት አካሄድና ደካማ የውሃ አስተዳደር ላይ የሚነሳ አጀንዳ ሆኗል።
ከዚህም በባሰ ግብፅ የላይኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት እንድም ልማት እንዳያለሙ በሴራ በማቀብ እርሷ ግን በአስዋን ግድብ ላይ የተመሠረተውን የናስር ሐይቅ ውሃ ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ በሚጠይቁ የሸንኮራ አገዳ፣ የጥጥና የሩዝ ልማቶች በማዋል ለብዙ ዓመታት በደል ስትፈጽም ኖራለች። ይህም የአሰዋን ግድብ የበደል ታሪክ ነው። አስዋን የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎትን፣ የውሃ ሀብትን በአንድ ወገን ላይ በማስቀመጥ የሌሎችን የልማት መብት የሚገድብ አስተሳሰብን የሚወክል ታሪካዊ ምልክት ሆኖ ቆይቷል።
ዛሬ ግን ይህ ትርክት ተለውጧል። ሕዳሴ ቀልብሶታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ -የቀጣናው የምስራች
በዓባይ ወንዝ ላይ አዲስ ምዕራፍ ተጽፏል።ሕዳሴ የተኛን ኃይል አንቅቷል። የተዘነጋን ሀብት ወደ ልማት ቀይሯል። የትናንትን ጥገኝነት ወደ የራስ አቅም አሸጋግሯል። ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ደጅ ወርቁን፣ አፈሩን፣ ግንዱንና ሌላውንም እያግበሰበሰ ሲጓዝ የኖረውን፣ ኢትዮጵያውያን ከኩበት ጭስ ጋር እየታገሉ፣ በጨለማ ስር ተቀምጠው በቁጭት ሲያዜሙለት የኖሩትን ዓባይን፣ ሕዳሴ ወደ ብርሃን ምንጭነት አዙሮታል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ 5 ሺህ 150 ሜጋዋት ኃይል ያመነጫል። በንጋት ሐይቅ ወደ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያከማቻል። ይህም የኢትዮጵያን ከውሃ ኃይል የሚመነጭ የኢነርጂ አቅምን በእጅጉ የሚያሳድግ፣ የኢኮኖሚ ልማቷን የሚደግፍ ትልቅ መሠረተ ልማት ነው።
የሕዳሴ የምስራችነት በዚህ አያበቃም።
የሕዳሴ ግድብ የቀጣናው የኢነርጂና የልማት ምንጭ ነው። ለሱዳን፣ ለጅቡቲ፣ ለኬንያ፣ ኃይል ማስተላለፍ ጀምሯል። ለሌሎችም ለመድረስ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል። የግድቡ መገንባት የጠቀመው እንጂ የጎዳው አካል የለም። የሱዳንን የጎርፍ አደጋ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና አለው። ለሱዳንም ሆነ ለግብፅ ከደለል ንጹህ የሆነ፣ ዓመታዊ ፍሰቱ የተስተካከለ ውሃ እንዲያገኙ ያስችላል።
የሕዳሴ ግድብ የሚገኝበት አካባቢ የአየር ሁኔታና ጂኦግራፊ እንደ እቶን በሚንተከተከው በረሃ ከተገነባውና ውሃን ያለቅጥ ከሚያተነው የአስዋን ግድብ አንጻር እጅግ ቀዝቃዛና ለውሃ ብክነትና ትነት ተጋላጭ ያልሆነ የውሃ ማከማቻ ነው። የንጋት ሐይቅም ጥልቅ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የውሃው የላይኛው ክፍል እጅግ ያነሰ የፀሐይ ተጋላጭነት አለው። ይህም ትነትን በእጅጉ የሚቀንስ ሲሆን፤ ለዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ከ10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ በላይ ውሃ በትነት እንዳይባክን ታድጓል።
ይህ ውሃ በደረቅ ወቅት፣ የበረሃ ቅንጦተኞቹን፣ የአዞ እንባ አፍሳሾችን እነግብፅንም ጭምር የሚያረሰርስ ነው።ሕዳሴ ዓባይን የፍትሐዊና የዘላቂ ልማት ምንጭ፣ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ዕድገት ምሰሶ እንዲሆን አዲስ መንገድ ከፍቷል።የሁለቱ ግድቦች ወግም ይኸው ነው። አስዋን ግድብ በሐይቅ ስር የኑቢያን ምድር ሲሰለቅጥ፤ የሚሊዮኖችን እርዛት የሚያስቀረውን ውሃ ሲያተን፣ ሌላው ግን በጨለማ የተዋጠውን በልማት ወደ ኋላ የቀረውን ቀጣና ከተኛበት ቀሰቀሰ፣ ብርሃኑን አዳረሰ። የልማት ተስፋ ሆነ።
ይኸው ነው!