አረንጓዴ ዐሻራ ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ሳቢ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ሳቢ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ ፤መስከረም 23/2019 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የሀገሪቱን የአረንጓዴ ልማት ግቦች ከማሳካት ባለፈ፣ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ እና ተስማሚ እያደረገ እንደሚገኝ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የጀመረችው ታሪካዊ የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ትልቅ አርአያ መሆን ችሏል።
በዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ተነሳሽነት አማካኝነት ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ 56 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ተችሏል።
በመርሃ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች ስነ-ምህዳርን ከማስጠበቅና ከተሞችን አረንጓዴ ከማላበስ ባለፈ ለምግብነት እና ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
ይህ ሁሉን አቀፍ ጥረት ሀገሪቱ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ጠብቃ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ብሩህ ጉዞ ጠንካራ እና አዲስ መሰረት ጥሏል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ አማን አሰፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከተሞች የሚካሄዱ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ስራዎች ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ዘመናዊና ማራኪ አድርጓቸዋል።
በከተሞች አካበቢ ከፍተኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መኖር እና የኢንዱስትሪ ማዕከል መሆናቸው ለከፍተኛ ካርቦን ልቀትና ብክለት ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ይህንን ችግር በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የሙቀት መጠንን በመቀነስ፣ የአካባቢ ስነ-ምህዳርን በመጠበቅ እና በከተሞች አካባቢ ጎርፍ እንዳይከሰት በመከላከል ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ አዎንታዊ ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት አዳዲስ የከተማ ፕላን አሠራር ላይ ማሻሻያ ማድረጉንም ተናግረዋል።
በዚህም አዲስ የሚዘጋጁ የከተማ ፕላኖች 30 በመቶ ለአረንጓዴ ልማት፣ 30 በመቶ ለመሠረተ ልማት እና 40 በመቶው ደግሞ ለመኖሪያነት እንዲውሉ የሚያስችል ሞዳሊቲ እንዲከተሉ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
በዚህ መሰረት የሚከናወኑ የከተማ ፕላን ዝግጅቶች የሀገሪቱን አረንጓዴ የልማት ግቦች ለማሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።