ኮደርስ ኢንሼቲቭ የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ኮደርስ ኢንሼቲቭ የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮ-ኮደርስ ኢንሼቲቭ የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ኢንሼቲቭ ዜጎች ተገቢው የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው በማድረግ ስራ እና ሀብትን በመፍጠር የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማጠናከር ተግባራዊ የተደረገ ፕሮግራም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ5 ሚሊየን የኮደርስ መርሐ ግብር ወደ 7 ሚሊየን ከፍ ለማድረግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ስዩም መንገሻ እንደገለጹት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ የስኬት ጉዞ በዋናነት ትልቁ የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ማጎልበት ነው።
የኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ሲጀመር አምስት ሚሊዮን ዜጎችን ስልጠና እንዲወስዱ መታቀዱን አንስተው፤ ከታቀደው በላይ ለማሳካት በመቻሉ ሰባት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ዜጎች ቁጥር 5 ነጥብ 4 ሚሊየን መድረሱን ገልጸው፤ በዚህም ክህሎታቸውን ማሳደግና በኦን ላይን የስራ እድል ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበታቸውን ተናግረዋል።
የኮደርስ ስልጠናው መሰረታዊ ነው፤ የዲጂታል ክህሎትን ለማሳደግ መንደርደሪያ፣ መስፈንጠሪያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድጉ ተግባራትን እያከናወነች መሆን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ዲጂታላይዜሽን በማስፋፋት ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎቶች ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውንም ገልጸዋል።
የዲጂታል ክህሎት ሀገርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ግብዓት በመሆኑ በዘርፉ ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኢትዮ ኮደርስ ዜጎች የዲጂታል ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸው፤ በቀጣይም እንደዚሀ አይነት ስልጠናዎች በላቀ ደረጃ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስታርትአፕ ዴቨሎፕመንት ኤክስፐርት አብይ ታደሰ በበኩሉ በኢትዮ ኮደርስና በሌሎች ኢኒሼቲቮች ስታርት አፖችን መደገፍ የሚችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የኮደርስ ስልጠና መሰረታዊ ክህሎትን ለማስጨበጥና የስራ ፈጠራዎችን ለማስፋፋት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኤ. ይ ዘርፍ የወጣቶችን ክህሎት የሚያዳብሩ ወደ ስታርት አፕ እንዲገቡ የሚያስችሉ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ነው የገለጸው።
ወጣቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ክህሎታቸውን ማሳደጋቸው ለስራ ፈጠራና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጿል።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሳይበር ሴኪዩሪቲ ኦዲተር ማርታ ሀዲስ አራቱንም ኮርሶች መውሰዳቸውንና በዘርፉ የነበራቸውን እውቀት ለማዳበር እንደጠቀማቸው ገልጸዋል።
ኢኒሼቲቩ ለወጣቶች በጣም ትልቅ እድል ነው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ክህሎትን ለማሳደግ ከወቅቱ ጋር ለመራመድ መሰረታዊ ስልጠና ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በሰው ሰራሽ የታገዙ ስራዎች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ገልጸው፤ ኮርሶቹ ለቀጣይ የስራ እድሎችና ሙያን ለማሳደግ መሰረት ነው ሲሉም ተናግረዋል።