ብሔራዊ ጥቅም - የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቀይ መስመር - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ጥቅም - የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ቀይ መስመር
ትልቅ ሀገር ፤ ትልቅ ሕዝብ ፣ ታላቅ ርዕይ
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ባለው የረዥም ዘመን ታሪክ በተለያዩ ታሪካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊና ውስጣዊ የፖለቲካ ሁነቶች ውስጥ አልፏል። የዓለም መንግሥታት ማኅበር ፣ በመቀጠልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች አባል በመሆን ለዓለም አቀፍ ሕግ የበላይነት፣ ለሉዓላዊነትና ለጋራ ደህንነት መከበር የጸና አቋም ስትሟገት ቆይታለች።
በዚህ መርህ መሰረት ባደረገ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዷ፣ ኢትዮጵያ ለፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መጠናከር፣ ለቀጣናዊ ወንድማማችነት እንዲሁም ለአፍሪካ ሀገራት የነፃነት ትግል ትልቅ ድጋፍ በማድረግ የአህጉሪቱ የነፃነትና የአንድነት ምልክት መሆን ችላለች። የዚህ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ውጤት በመሆንም፣ መዲናዋ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት (የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆን የአህጉሪቷ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነቷን አስመስክራ ቀጥላለች።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ ከህልውና፣ ነጻነት እና ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ጋር ተሳስሮ የዘለቀ የጽናት ጉዞ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለብሔራዊ ጥቅሟና ለሉዓላዊነቷ የማይደራደር ቀይ መስመር በመዘርጋት፣ የጂኦፖለቲካዊ ውጣ ውረዶችን በብልሃትና በጽናት ስትሻገር ቆይታለች። በዚህም መስመር ለዘመናት በዓለም አቀፍ መድረኮች ጥቅሞቿን አስጠብቃለች። ለሌሎች ጥቅምም ቆማለች።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ ስኬት ሆኖ የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል ነው። ይህ ድል፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ እኩል ሀገር እንድትታይና የዲፕሎማሲያዊ ገዢነት ምሳሌ እንድትሆን አድርጓታል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ከረጅም ታሪካዊ መሠረቱና የፓን-አፍሪካኒዝም ማዕከልነቱ ባልተራቀቀ መልኩ፣ አሁን ባለንበት ዘመን አዲስ የልማት፣ የሉዓላዊነትና የስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል። የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት መርሆዎች በአዲስ መነቃቃት ላይ ይገኛል። የዚህ አዲስ የዲፕሎማሲ እይታ ዋና መሠረት ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ጥቅምንና ሉዓላዊነትን ቀይ መስመር ያደረገ፣ ነገር ግን ለጎረቤት ሀገራት ሰላም፣ ልማትና የጋራ እድገት ቅድሚያ የሚሰጥ ተግባራዊ አቀራረብ ነው።
የመደመር መንግስት ዲፕሎማሲ አብሮ የመበልጸግ ፅንሰ-ሐሳብን ያቀነቅናል። ኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የሚረጋገጠው ጎረቤቶቿ ሰላምና ልማት ሲያገኙ ብቻ እንደሆነ በማመን "ቅድሚያ ለጎረቤት" የሚል መርህ ይከተላል። ይህ መርህ ከቀደመው ባህላዊ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ተሻግሮ ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ፣ ንግድና መሠረተ-ልማት ትስስር ተቀይሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጎረቤት ሀገራት መሪዎች በተለይም በቅርቡ ከኬኒያና ከጂቡቲ መሪዎች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች የአፍሪካ ቀንድን የማስተሳሰር ጥረት ማሳያ ናቸው። ይህ የኢኮኖሚ ትስስር በተጨባጭ የሚገጥም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬኒያ፣ ለጂቡቲና ለሱዳን በማቅረብ ቀጣናውን በኢነርጂ ድልድይ አስተሳስራለች።አዲስ አበባን ከጂቡቲ ወደብ የሚያገናኘው የባቡር መስመርና ወደ ኬኒያ (ላሙ ወደብ) የሚያቀኑት የላፕሴት (LAPSSET) ኮሪደር ፕሮጀክቶች የንግድ ፍሰቱን ለማሳለጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው።የጋራ የውሃ ሀብቶችን በጋራ የመጠቀምና ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ቀጠናዎችን የማስፋፋት ሥራዎች ተከናውነዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩ አበይት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የማትንበረከክና የማታወላውል አቋም አላት።ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ የጂኦፖለቲካዊና የዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ቢኖሩበትም፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቷን በማስከበር የግድቡን ግንባታና የውሃ ሙሌት በውጭ ጫና ሳታቋርጥ ከፍጻሜ አድርሳለች። ለዘመናት የቆየውን ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታ መሠረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ ዘላቂና ሕጋዊ የባህር በር ፍላጎቷን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን፣ ሉዓላዊነትና ግዛት አንድነቷን በተግባር የተጻረሩና አላስፈላጊ ጫናዎችን ለመጫን የሞከሩ አካላትን ዓለም አቀፍ ሕግንና ደንብን መሠረት ባደረገ መልኩ የመመከትና ምላሽ ለመስጠትም ወደ ኋላ የማትል መሆኗን በተግባር አሳይታለች።