አዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓልን የሚታደሙ እንግዶችን እየተቀበለች ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓልን የሚታደሙ እንግዶችን እየተቀበለች ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2019(ኢዜአ):- አዲስ አበባ ነገ በሚከበረው ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓልን የሚታደሙ እንግዶችን እየተቀበለች ነው።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ ያላት ናት።
ይህን ታላቅነቷን ከሚያረጋግጡ ሀብቶቿ መካከል ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶቿ፣ ባህሎችና የቱሪስት መስህቦቿ ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህ መካከልም ከገዳ ስርዓት የሚመነጨው ኢሬቻ አንዱ ነው።
ኢሬቻ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ኹነቶች በአደባባይ የሚከበር ሲሆን፤ ዘንድሮም ነገ በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።
ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ላይ የሚታደሙ ተሳታፊዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ህብረ ዝማሬዎች በማሰማት እና ልዩ ልዩ ባህላዊ ክዋኔዎችን በማሳየት ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ።
የኢዜአ ሪፖርተሮች በአዲስ አበባ ቅኝት ባደረጉባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ነገ በሆራ ፊንፊኔ የሚከበረውን ኢሬቻ በዓል ለመታደም የመጡትን እንግዶችን ከተማዋ እየተቀበለች ነው።
በበዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶች የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያገኙባቸው አካባቢዎችም ተዘጋጅተው ወደ ስራ ገብተዋል።