ኢሬቻ የአንድነትና የእርቅ እሴትን የሚያጠናክር ነው – አባ ገዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ የአንድነትና የእርቅ እሴትን የሚያጠናክር ነው – አባ ገዳዎች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2019(ኢዜአ):- ኢሬቻ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የሰላም እሴቶችን ለማጠናከር አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን አባ ገዳዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ ያላት ሀገር ናት።
ይህን ታላቅነቷን ከሚያረጋግጡ ሀብቶቿ መካከል ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶቿ፣ ባህሎችና የቱሪስት መስህቦቿ ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህ ባህላዊ ሀብቶቿ መካከል ደግሞ ከገዳ ስርዓት የሚመነጨው የኢሬቻ በዓል ተጠቃሽ ነው።
ኢሬቻ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ሁነቶች በአደባባይ የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም ነገ በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም ከነገ በስትያ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።
የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው አባ ገዳ ጉጂ ጃርሶ ዱጎ፣ ኢሬቻ ማህበረሰቡ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት፣ ይቅር የሚባባልበትና በጋራ የሚመካከርበት የአንድነት በዓል ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ኢሬቻ በተለይ የአንድነትና የፍቅር መልዕክቶች የሚንጸባረቁበት መሆኑን ጠቁመው፤ የበዓሉ ታዳሚዎች በአንድነት መንፈስ ማክበር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ከባሌ ዞን የመጡት አባ ገዳ አብዱባሻ መሐመድ በበኩላቸው፣ ኢሬቻ ባህልንና ታሪክን ከማስተዋወቅ ባሻገር ለቱሪዝምና ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን አስተዋፅኦ ጠቁመዋል።
ኢሬቻ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚመጡ ጎብኚዎችን በማሰባሰብ የባህል ልውውጥንና የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማሳደግ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።
ኢሬቻ ከአባቶችና ከእናቶች የተላለፈ የምስጋና ባህል መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰዎች ወደ ኢሬቻ ከመምጣታቸው በፊት ከተቀያየሙት ሰው ጋር ይቅርታና እርቅ በመፈጸም ማክበር እንደሚገባ ያስገነዘቡት ደግሞ አባ ገዳ አዲሱ ሽብሩ ናቸው።
አባ ገዳዎቹ እንደገለጹት የኢሬቻን የአብሮነትና የፍቅር እሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ባህሉን ማስቀጠል ይገባል።