በክልሉ እድሜያቸው የደረሰ ህፃናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት መረባረብ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ እድሜያቸው የደረሰ ህፃናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት መረባረብ ያስፈልጋል
ባህር ዳር፣ መስከረም 22/2019(ኢዜአ):- በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ በጉባኤው ማጠናቀቂያ እንዳሉት፤ በክልሉ የመማር ማስተማር ሥራውን ምቹና የተሻለ ለማድረግ የንቅናቄ ሥራ ተጀምሯል።
ለዚህም በክልሉ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በመማር ማስተማር ሥራው ላይ የደረሰውን ጫና መቀልበስ የሚያስችሉ ተግባራት በተቀናጀ አግባብ እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል በኩል ሰፊ ሥራ መሠራቱን አንስተው፣ በተያዘው ዓመትም በስምንት ዋና ዋና ከተሞች ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል ብለዋል።
ትምህርት ለሁሉም የልማት አቅሞች መነሻ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለዚህም ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
በዚህ የትምህርት ዘመን በክልሉ ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ርብርብ እየተደረገ ሲሆን እስካሁን 70 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
ባለፈው የትምህርት ዘመን 59 በመቶ ተማሪዎችን ማስተማር እንደተቻለ አስታውሰው፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመን እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ወደ ትምህርት ገበታ ያልመጡ እና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ሕፃናት ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመጡ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም ምሁራን፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ወላጆች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችን ጨምሮ መላው ማኅበረሰብ እገዛና ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋለውን ፍትሐዊነትና ተደራሽነት ችግር የሚያቃልሉ ሥራዎችም ይከናወናሉ ብለዋል።
የምክር ቤት አባላትም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት የትምህርት ዕድል ተቋዳሽ እንዲሆኑና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የጎላ ሚናቸውን እንዲወጡ የላቀ ጥረት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ማጠናቀቁ ይታወቃል።