ቀጥታ፡

የባህል አልባሳት ዲዛይን የሸማቹን ፍላጎት በማርካት የንግድ እንቅስቃሴውን እያነቃቃ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2019(ኢዜአ):-ለኢሬቻ በዓል የቀረበው አዳዲስና ዘመናዊ የባህል አልባሳት ዲዛይን የሸማቹን ፍላጎት በማርካት የንግድ እንቅስቃሴውን እያነቃቃ መሆኑ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ ያላት ሀገር ናት። 

ይህን ታላቅነቷን ከሚያረጋግጡ ሀብቶቿ መካከል ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶቿ፣ ባህሎችና የቱሪስት መስህቦቿ ተጠቃሽ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከልም ከገዳ ስርዓት የሚመነጨው ኢሬቻ አንዱ ተጠቃሽ ነው። 

ኢሬቻ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ሁነቶች በአደባባይ የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም ነገ በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም ከነገ በስትያ  ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።

በኢሬቻ በዓል ዋዜማ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሱቆች አይነተ ብዙና ማራኪ ዲዛይን ባላቸው ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቀው ይታያሉ።

የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የባህላዊ አልባሳት መሸጫ ሱቆች የሸማቾችን ቀልብ የሚስቡ የኢትዮጵያውያን ውብ እጅ ስራዎች ግብይት ደርቷል።

ነጋዴዎችና ደንበኞች የባህል አልባሳት በዓይነትና በመጠን በገበያው ላይ መቅረባቸው ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ገበያውን እያነቃቁ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በባህል አልባሳት ንግድ ላይ የተሰማሩት ሮባ ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባህላዊውን ከዘመናዊው የእጅ ሥራ ጋር ያቀናጁ የባህል አልባሳት በገበያው በስፋት ቀርበዋል።

የባህል አልባሳቱ የኦሮሞ ህዝብ ባህል ይበልጥ እንዲያድግና ህብረተሰቡ ለባህሉ እድገት ፍላጎት እንዲያሳድር ከማድረጉም በላይ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ነጋዴ አለሚቱ ደንደና በበኩላቸው፤ የኢሬቻ በዓል ድባብ ገበያውን እያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።

በየዓመቱ የሚወጡ አዳዲስ የሀገር ባህል አልባሳት ዲዛይኖች ተፈላጊነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ በሸማቾች ምርጫ በተመጣጣኝ ዋጋ በተለያዩ ዲዛይኖች ለህጻናትና አዋቂዎች ቀርበዋል ብለዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሀገር ባህል ልብስ ግብይት ላይ ያገኘነው ወጣት ቶለሳ ሽጉጤ፤ የባህል አልባሳቱ የኦሮሞን ህዝብ ታሪክና ባህል የሚገልጹ፣ በተለያዩ ዲዛይን በከፍተኛ ጥራት የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጿል።

ወጣት ኪያ በጂጋ በበኩሉ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ከሚያከብራቸው በዓላት አንዱ መሆኑን ገልጾ፤ በየዓመቱ በተለያዩ ዲዛይኖች የሚዘጋጁ የሀገር ባህል አልባሳት ተወዳጅነትን አትርፈዋል፤ በዓሉንም በደስታ እንድናከብር አስተዋጽኦ አድርገዋል ብሏል።

የባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው በተመጣጣኝ ዋጋ ሳቢና ዘመናዊ ሆነው ለገበያ በመቅረባቸው ህብረተሰቡ ደስ ብሎት እየገዛቸው መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ደገፋ ኃምቢሳ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም