ከአባይ እስከ ቀይ ባህር - የኢትዮጵያ አይበገሬነት እና የግብጽ ሴራ - ኢዜአ አማርኛ
ከአባይ እስከ ቀይ ባህር - የኢትዮጵያ አይበገሬነት እና የግብጽ ሴራ
ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ የብዙ ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎች ማዕከል ሆና የቆየች ሀገር ናት።ሀገሪቱ ያሏትን ተፈጥሮአዊ ሀብቶች እንዳትጠቀም ፣የጂኦፖለቲካዊ አሰላለፍ ውስጥ የሚገባትን ቦታ እንዳትይዝ ለዘመናት የተደራጀ እና የተቀናጀ ሴራ እና ጫና ሰለባ ሆናለች።
ከእነዚህ ዘመናትን ከተሻገሩ ሴራዎች ጀርባ ደግሞ ግብጽ ትገኛለች።
የግብፅ አቋም እና የውጭ ፖሊሲ በዋናነት የሚያተኩረው የዓባይን ወንዝ ውኃ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የተረጋጋች፣ጠንካራ እና በኢኮኖሚ የበለጸገች ኢትዮጵያ እንዳትፈጠር በማድረግ ላይ ነው።
ግብፅ ይህን ዓላማዋን በተለያዩ ጊዜያት በቀጥታ በጦርነት ለማስፈጸም ያደረገችው ጥረት በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ሽንፈት ተከናንባ እንድትመለስ አድርጓታል።ይህ አልሳካ ሲላት ደግሞ የኢትዮጵያን የውስጥ ተቃዋሚዎች እና አማጺ ቡድኖችን በመደገፍ ሀገሪቱን የማዳከም ስልት ስትከተል ኖራለች።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባሉት አስርት ዓመታት፣ ግብፅ በአፍሪካ እና በአረብ ዓለም ውስጥ ተፅዕኖዋን ለማስፋት ስትጥር፣ የዓባይ ተፋሰስን እና ቀይ ባሕርን ለደህንነቷ እንደ ዋና መሠረት አድርጋ ተመልከታቸዋለች።ኢትዮጵያ፣ በዓባይ ወንዝ ላይ ያለች ትልቅ እና እየጎለበተች ያለች ሀገር በመሆኗ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም ሴራዋን አጠናከረች።ለዚህም ዓላማ ስኬት በሰሜን ኢትዮጵያ የተዳፈነ እሳት ማስቀመጥ ነበረባት።ኤርትራን ለመገንጠል፤ ጉዳይ ፈጻሚውን ሻዕቢያን መመስረት ግቧ አደረገች።
የኤርትራ ነፃነት ግንባር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1960 በካይሮ በተሰደዱ የኤርትራ ፖለቲከኞች እና ተማሪዎች ተመሠረተ። በዚህ ሂደት ግብፅ የኤርትራ የመገንጠል እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ፖለቲካዊ ምህዳር የፈጠረች ሲሆን፣ የግብፅ ሚዲያዎች ደግሞ ለእዚህ እኩይ ዓላማ የሚያግዝ ፕሮፓጋንዳ አሰራጮች ነበሩ።
በዚህ አሰላለፍ ውስጥ ሻዕቢያ የግብፅ ዋና ስትራቴጂካዊ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል። ግብፅ ለሻዕቢያ አስፈላጊውን ወታደራዊ፣ የገንዘብ እና የዲፕሎማሲያዊ ሽፋን በመስጠት በሰሜን ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ለተካሄደው ውጊያ ስንቅ እና ትጥቅ እንዲያገኝ አድርጋለች።
የኤርትራ መገንጠል ዋነኛ ውጤት ኢትዮጵያ ታሪካዊ የባህር በሮቿን አጥታ የተዘጋች ሀገር እንድትሆን ማድረግ ነበር። ይህ ደግሞ የግብፅን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ያሳካ እርምጃ ሆኗል።
ለዚህ እኩይ ዓላማ ለተወለደው ቡድን ደግሞ ቀጥተኛ የገንዘብ፣ የወታደራዊ እና የስልጠና ድጋፍ የመስጠት ፖሊሲን ተከትላለች።በግብፅ ስሌት፣ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ አካላት የሚደረገው ድጋፍ በተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት ላይ ጫና ለመፍጠር ይረዳል የሚል ነው።በመጠኑ የተሳካለት ቢመስልም ያሰበችውን ማግኘት አልቻለችም።ብርቱዋ ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አሳክታ አጀንዳዋን ቀይ ባህር ላይ አድርጋለች።
ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ፖለቲካዊ ጫና እንደ ጠቃሚ መንገድ አድርጋ ቀጠለችበት። ግብፅ ከሻዕቢያ ባለፈ ለሀገር ውስጥ ታጣቂዎች ድጋፍ በመስጠት የተወሰኑ የትንኮሳ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ረድታለች። አስመራ በታሪክ በተረጋገጠ መልኩ የፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴዎች ሁሉ መነሻ እና ማዕከል ሆና አገልግላለች። ስውሩ ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መተግበር እንዳትችል አደረጋት። የተረጋጋች ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ አንጻር የራሱን መጥፎ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
አሁንም ግብጽና ሻዕቢያ በቀረጹት ኢትዮጵያን የማዳከም ሥራ ላይ ሕገ-ወጡ ሕወሓት በዋና ተላላኪነት እና ጉዳይ ፈጻሚነት ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ሕወሓት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሻዕቢያ የፖለቲካ እና የወታደራዊ ሥልጠና ሲያገኝ ነበር።ሕወሓት ሥልጣን በያዘበት ወቅት፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት መብት ከሕግ አግባብ ውጭ አሳልፎ በመስጠት የሻዕቢያን እና የግብፅን ዓላማ በተሻለ መልኩ አሳክቷል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ ምክንያት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለወደብ ኪራይ እንድታወጣ ተገዳለች። ይህም የኢኮኖሚ እድገቷን የገታ እና ለውጭ ጥገኝነት የዳረጋት ዋነኛ ምክንያት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አካባቢ ኢትዮጵያ የነበራትን ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ የበላይነት እንድታጣ አድርጓታል።
የውስጥ አለመረጋጋት እና ጦርነቶች ዓባይን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቿን በጊዜው እንዳትጠቀም እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል። አሁንም ቢሆን ግብፅ ከኢትዮጵያ አልፋ የአፍሪካ ቀንድን ወደ አንድ ግዙፍ የጦር ሜዳ ለማሸጋገር ለሚሰሩ ወገኖች ይፋዊ ወታደራዊና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ በመስጠት ቀጣናዊ ስጋት መደቀኗን ቀጥላበታለች።]
ኢትዮጵያ ለዘመናት በወራሪዎችና በውጭ ተጽዕኖዎች ሳትንበረከክ ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረችበት ምስጢር፣ ታሪካዊ ጥንካሬዋንና የሕዝቦቿን አንድነት መሠረት ባደረገ ጽናት ነው። ግብፅ የኢትዮጵያን ግዛት ለመያዝ ያደረገቻቸው ተደጋጋሚ የወረራ ሙከራዎች በጉራዕና በጉንደት አውደ ውጊያዎች በኢትዮጵያውያን ጀግንነት ተመክተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በወገንተኛ ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ለዘመናት ሲሰራጩ የቆዩ ሀሰተኛ መረጃዎችና የሳይኮሎጂካል ጦርነቶች በኢትዮጵያ እውነተኛ ዲፕሎማሲ ተሸንፈዋል ። አሁንም የግብፅና የኤርትራ (የሻዕቢያ) ወቅታዊ ስትራቴጂካዊ አሰላለፍም ሆነ የሕወሓት ተላላኪነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጊዜያዊ ፈተናዎች ሆነው የሚያልፉ አኩይ ተግባራት እንጂ የኢትዮጵያን የሺህ ዓመታት የሀገርነት መሠረት ሊያናጉ አልቻሉም።
ከዚህ አኳያ ያለፈውን ታሪክ በጥልቀት መረዳት፣ የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ መገንዘብና የጥፋት አሰላለፎችን ማወቅ የዛሬዋንና የነገዋን የበለጸገችና የተከበረች ኢትዮጵያ ለመገንባት፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ወሳኝና መተኪያ የሌለው መንገድ ነው።
ኢትዮጵያ ለታሪካዊ ጠላቶቿ በየትኛውም መልኩ የማትንበረከክ ጽኑ አገር መሆኗን ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ታረጋግጣለች!