ኢሬቻ የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት የሚያጠናክር ታላቅ ሀገራዊ እሴት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት የሚያጠናክር ታላቅ ሀገራዊ እሴት ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2019(ኢዜአ):-ኢሬቻ የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት የሚያጠናክር ታላቅ ሀገራዊ እሴት መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ ያላት ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ ወንድምና እህትማማችነትን የሚያጠናክሩ ውብ እሴቶች ያሏት ሀገር ናት።
የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል በማስመልከት "ኢሬቻ፤ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሃሳብ 8ኛው የኢሬቻ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በፎረሙ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ በሕብር ተሸምነው ያሸበረቁ ቱባ ባህሎች፣ እሴቶችና ማንነቶችን የተጎናጸፈች ሀገር ናት ብለዋል።
የኢሬቻ በዓልም ከኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት የሚቀዳ የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ የሆነ የአደባባይ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ አንድነት፣ ወንድምና እህትማማችነትን የሚያስተሳስር የሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉም ባህላዊ እሴትና መገለጫዎቹ ሳይበረዙና ሳይከለሱ ለትውልድ በማስተላለፍ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አንስተዋል።
የሀገራችንን ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የኢሬቻ በዓል የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደ ኢሬቻ ያሉ በአደባባይ የሚከበሩ በዓላትን በማልማትና በመንከባከብ የቱሪዝም ዘርፍ ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።