በክልሉ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ባህር ዳር ፤ መስከረም 22/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለፁ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 7ኛ ዙር፣ 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን መስራች እና 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ ያደርጋል።
በዚህ በጀት ዓመት ለነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንዲሁም ለሌሎች ስራዎች ከ31 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በጀቱ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወሳኝ ፕሮጀክቶች በውጤታማነትና በፍትሃዊነት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
በተለይም የከተማና የገጠርን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ የመንገድ መሰረተ ልማቶች በተገቢው ሁኔታ ይፈጸማሉ ብለዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግ በኩልም በርካታ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማሳለጥና የግብርና ዘርፉን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚያግዙ የመስኖ ተቋማት ፕሮጀክቶች ግንባታም በተጠና መንገድ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።
የኃይል አቅርቦት ክፍተትን ለማቃለልም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከመነጋገር ባለፈ አማራጭ የኃይል አቅርቦቶችን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግም ተኪ ምርትም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሌሎች ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት ዘርፉን የማሳደግ ስራ ትኩረት እንደተሰጠውም አመልክተዋል።
የልማት ስራዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ የምክር ቤት አባላት አበክረው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በሁሉም ዘርፍ የቀረቡ እቅዶች በውጤታማነት ተፈጻሚ እንዲሆኑ የምክር ቤት አባላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ይወጣሉ ብለዋል።