ቀጥታ፡

የክልሉ መንግሥት በመደመር እሳቤ የሕዝቡን ባህልና እሴት ለተከታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2019(ኢዜአ):- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በመደመር እሳቤ የሕዝቡን ባህልና እሴት ለተከታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ሲሉ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

8ኛው የኢሬቻ ፎረም “ኢሬቻ ፡ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሐሳብ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በሸራተን አዲስ እየተካሄደ በሚገኘው የኢሬቻ ፎረም ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የመደመር መንግሥት የሕዝቡ ባህልና እሴት እንዲጎለብትና ለተከታዩ ትውልድ እንዲተላለፍ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ባህልና አንድነት ማሳያ፣ የሰላምና የመግባባት ማረጋገጫ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባትና እድገትም ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሕዝቡን ሀገር በቀል እውቀትና የመደመር እሳቤን  መሠረት በማድረግ የባህል ተሃድሶ ሥራ እያካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በዚህም ህዝቡን በኢኮኖሚ የመገንባት፣ በቴክኖሎጂ የማብቃት፣ በኪነ-ጥበብና በሜዲያ በመደገፍ የሚገባው ደረጃ ላይ ለማድረስ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት በኢሬቻ በዓል አማካኝነት የሕዝቡን ባህል፣ እሴትና ማንነት ወደ ተገቢው  ቦታ ለመመለስና በአንድነት መንፈስ ለላቀ ስኬት ለመብቃት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም ያረጋግጣል ብለዋል።

የ2019 የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል የኦሮሞን ባህል፣ እሴትና ማንነት በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አቶ ሽመልስ አሳስበዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢሬቻ በዓል ህዝቡ የክረምቱን ጨለማ አልፎ ለብርሃን  በሰላም ስላደረሰው አምላኩን የሚያመሰግንበት የምስጋና በዓል ነው ብለዋል።

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በጥሩ ሁኔታ እንዲከበር የኢሬቻ ማከበሪያው አካባቢ መልማቱን የገለጹት ከንቲባዋ፤ የኢሬቻ በዓል እሴቶች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የኢሬቻ ፌስቲቫል በኢትዮጵያና በአፍሪካ ደረጃ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ለዓለም ትልቅ ልምድ የሚሰጥ ታላቅ መድረክ መሆኑን ገልጸው፤ የአዲስ አበባ ከተማም በየዓመቱ በአምስቱ በሮች የኢሬቻን እንግዶች ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያ፣ ኦሮሞ ለዓለም የኢሬቻ ሥርዓትን ያበረከተ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢሬቻ የክብር ሥርዓትና የአንድነት እንዲሁም የእህትማማችነትና ወንድማማችነት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓል አከባበር ብዙ ውጣውረዶችን  አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱ ለህዝባችን ታላቅ ድል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም