የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማንጸባረቂያ - የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማንጸባረቂያ - የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት
አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2019 (ኢዜአ)፦የዳመርጆግ - ደወሌ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከማፋጠን ባለፈ ሀገሪቷ ከጅቡቲ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ በመሰነቅ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋች ትገኛለች።
በጅቡቲ ዳመርጆግ እና በኢትዮጵያ ደወሌ መካከል የሚገነባው የ120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገቷን ለማፋጠን ከጀመረቻቸው የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳል።
የፕሮጀክቱንም ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ እና የዳንጎቴ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አሊኮ ዳንጎቴ በቅርቡ አስጀምረዋል።
ፕሮጀክቱም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረገ አጋርነት የሚተገበር ሲሆን፤ ከአንድ ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር በላይ የተጣራ የነዳጅ ምርቶችን የመያዝ እና የማስተላለፍ አቅም እንደሚኖረው የግንባታው ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ መገለጹ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት እና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በቅርቡ ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ነዳጅን ለማስገባት የተሽከርካሪ አማራጮች የምትጠቀም መሆኗ አስተማማኝ የሆነ የነዳጅ አቅርቦት እንደ ሀገር እንዳይኖር እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ-ጅቡቲ በሁለቱ ሀገራት የዳመርጆግ-ደወሌ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባታ መጀመር የሀገሪቷን የነዳጅ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚረዳ ተናግረዋል።
አንድ ኢንቨስትመንት ፋይዳው የሚለካው በኢኮኖሚ ላይ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለዜጎች በሚፈጥረው የስራ እድል ጭምርም መሆኑን በማንሳት የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቱ ከዚህ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነም አብራርተዋል።
ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ምሁር ብርሃኑ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሀገሪቷ የሚከናወኑ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ እንደ ሀገር የነዳጅ ክምችትን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የዳመርጆግ-ደወሌ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት አስተማማኝ እና በተለያዩ ምክንያቶች የማይዋዥቅ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለአምራች ኢንዲስትሪዎች የነዳጅ አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ የመስጠት አቅምን የሚያሳድግ፣ ለመካናይዝድ ግብርና ምርታማነት ለትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት ትልቅ ሚና ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ አብራርተዋል።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ አቅዳ የምታከናውናቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የራሷን ኢኮኖሚያዊ እድገት ከማረጋገጥ ባለፈ ለአሁጉሪቷ እድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የጀመሩት ፕሮጀክትም እንደ ማሳያነት መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት የተጀመረው ፕሮጀክት የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ይበልጥ የሚያጠናክር ነውም ብለዋል።