ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የፖሊሲ እርምጃዎች ዓለም አቀፍ የባንክና የፋይናንስ ተቋማትን ኢንቨስትመንት የሚያበረታቱ ናቸው

አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የፖሊሲ እርምጃዎች የሀገር ውስጥ ባንኮችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ዓለም አቀፍ የባንክና የፋይናንስ ተቋማትን ኢንቨስትመንት የሚያበረታቱ መሆናቸውን የግሎባል አልያንስ ፎር ባንኪንግ ኦን ቫልዩስ ዋና ዳይሬክተር ማርቲን ሮነር ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የፋይናንስ ኢንዱስትሪው እንዲያንሰራራ እያደረገ ነው።

በዚህም ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ ያላት ኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ ታሪካዊ ዕድልን ከፍቷል።

የግሎባል አልያንስ ፎር ባንኪንግ ኦን ቫልዩስ ዋና ዳይሬክተር ማርቲን ሮነር ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስፋት ክፈተኛ አቅም አለው።

በሀገር በቀል የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ክፍት መደረጉም የኢትዮጵያን ዕምቅ አቅም መጠቀም ለሚሹ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ወርቃማ ዕድል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትም ዓለም አቀፍ የባንክና ፋይናንስ ተቋማት ኢንቨስት የሚያደርጉበትን አስቻይ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።

የፋይናንስ ዘርፍ ለኢንቨስትመንት ክፍት መደረጉም የሀገር ውስጥ ባንኮችን የተወዳዳሪነት አቅም በማጎልበት ጥራትና ብቃት ለው አገልግሎት የሚሰጡበትን ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተከናወኑ መጠነ ሰፊ ዘመናዊ የፋይናንስ ዘርፍ የፖሊሲ እርምጃ ዘመኑ የሚጠይቀውና አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃም የፋይናንስ ዘርፉን በትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ የሚመራበትን ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን አመላክተዋል።

ለአብነትም የካፒታል ገበያ፣ የገንዘብና የውጭ ምንዛሬ የፖሊሲ እርምጃዎች ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ የባንክና የፋይናንስ ተቋማት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መዋቅራዊ የፋይናንስ ዘርፍ ፖሊሲ እርምጃም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ከፍታ ብሩህ ጊዜ እንደሚጠብቀው አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል።

በጥቂት ዓመታት ውስጥ የታየው ውጤት ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውን ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም