ቀጥታ፡

የዘላቂ ሰላም ግንባታና የልማት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ የጋራ አጀንዳችን ነው

ጎንደር፣ መስከረም 22/2019 (ኢዜአ) ፡-የሀገር ብሄራዊ ጥቅም፣የዘላቂ ሰላም ግንባታና የልማት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ የጋራ አጀንዳችን ነው ሲሉ የጎንደር ከተማና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተገን ደረጀ ገለፁ።

በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሒደዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጎንደር ከተማና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተገን ደረጀ፤ በጎንደር ከተማ እና አካባቢው በመከናወን ላይ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን አድንቀዋል።


 

በተለይም የኮሪደር ልማት፣ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት፣ የቅርሶች እድሳትና ጥበቃ እንዲሁም ሌሎች ልማቶችን በማንሳት እመርታና ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሀገር ብሄራዊ ጥቅም፣ የዘላቂ ሰላም ግንባታና የልማት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ የጋራ አጀንዳችን በመሆኑ በአብሮነትና በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

በጎንደር ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ስራ አስፈጻሚ አቶ ዝናህወርቅ ታደሰ፤ በበኩላቸው የሀገር ልማትና እድገት የሚረጋገጠው በዜጎች ሁለንተናዊ ትብብርና ትጋት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም በፖለቲካ ረገድ የሃሳብ ልዩነት ቢኖርም በሀገር ሉአላዊነት፣ በልማትና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያለምንም ልዩነት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዚህም ፓርቲያቸው ጠንካራ አቋም ያለው መሆኑን አንስተው ለሀገር ሰላም፣ ልማትና የዜጎች ተጠቃሚነት ይበልጥ ተቀራርበን እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የጎንደር ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ምትኩ አንዳርጌ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላም፣ በልማትና በብሄራዊ ጥቅም ላይ ከመንግስት ጋር በመተባበርና ይበልጥ በመቀራረብ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በከተማዋ እየተካሄደ ያለውን ልማትና ዘላቂ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የወጣቶች ማህበራትና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም