ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው የመድኃኒት ማምረቻ ማዕከል እየሆነች ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአካሄደቻቸው የፖሊሲ ለውጦች በቀጣናው የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረቻ ማዕከል እያደረጋት መሆኑን  የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ገለጸ።      

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ በመሰነቅ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋች ትገኛለች።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ በሽታን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ ፖሊሲ በመከተል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን በዘርፉ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤መድኃኒትን በሀገር ውስጥ ለማምረት እንደሀገር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ዘርፉን እያነቃቃው ነው።   

በቅርቡ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የተቀላጠፉ የቁጥጥር ሥርዓቶች እና እየጨመረ የመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት ለሀገር ውስጥ መድኃኒት ምርት እጅግ ተስማሚ ሁኔታን መፍጠራቸውን ገልጸዋል።  

ለመድኃኒት ምርት የሚያስፈልጉ እንደ ውሃ፣ ተስማሚ የአየር ሁኔታ፣ ሰፊ የገበያ ዕድልን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መኖሩ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓት ሌሎች ምክንያቶች መሆኑን ጠቅሰዋል።  

የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ መድሃኒት አምራቾችን እየሳበ ያለ ትልቅ መሰረተ ልማት መሆኑን ጠቁመው፤ይህም ከውጪ የሚመጣውን ኢንቨስትመንት የማሳለጥ አቅም  እየፈጠረ ነው ብለዋል።      

መድኃኒት አምራቾች ለ7 ተከታታይ ዓመት የኮንትራት ሥምምነት ፈርመው መድሃኒት ማቅረብ የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱም ሀገር ውስጥናት የውጭ ባለኃብቶችን እየሳበ ያለ ውጤታማ አሰራር መሆኑን ጠቅሰዋል።    

ሥምምነቱ አምራቾች መድሃኒት ለማቅረብ በቂ ግዜ የሚሰጣቸው ነው ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ ይህም አምራቾች ምርት ላይ እንዲያተኮሩ በማድረግ ምርታማነትን የሚያሳድግ አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።  

ለመድኃኒት ምርት ጥራት የተሰጠው ትኩረትም የዓለም ጤና ድርጅት የሚያስቀምጠውን የመልካም አመራረት መስፈርት የሚያሟሉ የመድኃኒት አምራቾች ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ ማስቻሉንም አብራርተዋል። 

በአሁኑ ወቅት 7 ዓለም አቀፍ የመልካም አመራረት መስፈርትን የሚያሟሉ አምራቾች መኖራቸውን የገለጹት ዶክተር ዳንኤል፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ሀገራዊ የመድሃኒት አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር አመላካች ውጤቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።  

በዘርፉ የተተገበሩ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች ኢትዮጵያ በቀጣናው የመድኃኒት ማምረቻ ማዕከል የሚያደርጋት ቁመና ላይ እንድትገኝ አስችሏታል ሲሉም ተናግረዋል።    

እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥርን ተከትሎ የመድኃኒት አቅርቦት ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህን ፍላጎት በሀገር ውስጥ አቅም ለማቅረብ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለዚህ ደግሞ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበርም የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም