በክልሉ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)
አርባ ምንጭ ፤ መስከረም 22/2019 (ኢዜአ) ፦የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክልሉ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ገለፁ።
ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር የክልሉን ልማት አንድነትና ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በመደመር መንግሥት መርህ የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ በቅንጅት እንደሚሰራና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንደሚጠናከሩ ተናግረዋል፡፡
ደቡብ ኢትዮጵያ ብዝሃ ማንነት ያለው ክልል እንደመሆኑ የህዝቡን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ወንድማማችነትና እህትማማችነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
ክልሉ ሰፊ ፀጋ ያለው መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ መሰረታዊ ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ የገጠርና ከተማ ኮሪደር፣ የሌማት ትሩፋትና አረንጓዴ አሻራ የክልሉ የትኩረት መስኮች መሆናቸውንና በትምህርትና ጤና ልማትም የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሌላኛው ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመንግስት አገልግሎቶች በዲጂታል ስርአት በመታገዝ የተገልጋዩን እርካታ ማረጋገጥ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በመታገል ክልሉን የዕድገትና የብልጽግና ሞዴል ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አባላት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ኃላፊነታቸውን እንድወጡም ጠቁመዋል።