የኢትዮጵያና አርሜኒያ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ የንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ አጋርነት እየተሸጋገረ ነው - አምባሳደር ሳሀክ ሳርጊሲያን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና አርሜኒያ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ የንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ አጋርነት እየተሸጋገረ ነው - አምባሳደር ሳሀክ ሳርጊሲያን
አዲስ አበባ፤መስከረም 22 /2019(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና አርሜኒያ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ የንግድና ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑን የአርሜኒያ አምባሳደር ሳሀክ ሳርጊሲያን ገለጹ።
የመደመር መንግሥት ገቢር ነበብ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከባህላዊ የዲፕሎማሲ አሰራር በመላቀቅ ከውስጥ የሚነሳ ቅድሚያ ለጎረቤት፣ ለአፍሪካና ለዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በመስጠት የሚሻገር ነው።
በዚህም ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ ያላት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርህ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ትብብርን በማጎልበት ብሔራዊ ጥቅምንና ፍላጎትን እያስጠበቀ ይገኛል።
ከሀገራት ጋርም የጋራ ተጠቃሚነትን በማጎልበት፣ በትብብርና አብሮ በማደግ ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን በመትከል በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ውጤታማ የዲፕሎማሲ አካሄድ ማራመዷን ቀጥላለች።
በዚህም ከሀገራት፣ ከቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር ያላትን ትብብር በማጎልበት የዲፕሎማሲ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከልነቷን እያጎለበተ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የአርሜኒያ አምባሳደር ሳሀክ ሳርጊሲያን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና አርሜኒያ ወዳጅነት በሃይማኖታዊና ተያያዥ የግንኙነት መስኮች ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው።
የሀገራቱን የዲፕሎማሲ ወዳጅነትም አርሜኒያ ከስድስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በከፈተችው ኤምባሲዋ አማካኝነት የጋራ ትብብርና ተጠቃሚነትን የማጎለበት ሥራ እየሰራች ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮ-አርሜኒያ መካከል ጠንካራ የፖለቲካ ግንኙነት በመገንባት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብርን የሚያጎለብት መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።
የአርሜኒያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ባካሄዱት የተለያዩ ይፋዊ የሥራ ጉብኝቶችም የሀገራቱን የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጎለብቱ ፍሬያማ ምክክር ከኢትዮጵያ አቻቸው ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
በዚህም በኢትዮ-አርሜኒያ መካከል የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የትምህርትና ስልጠና የትብብር አድማሶችን ማስፋት የሚያስችል የጋራ መግባባት መፈጠሩን አብራርተዋል።
በስድስት ወራት ብቻ ከ10 በላይ የአርሜኒያ የባለሀብቶች ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን አስታውቀዋል።
ለዚህም የአርሜኒያ የኢንቨስትመንት ተቋም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር ውጤታማ የበይነ መረብ ምክክር ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
ኤምባሲውም የሀገራቱን የንግድ ምክር ቤቶችና የዲያስፖራ ጉዳዮች አቻ ተቋማትን በማገናኘት የሀገራቱን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጎልበት ስምምነት በመፈራረም ጭምር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ መልኩም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በሙዚየም፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የትምህርትና ሥልጠና ትብብር መስኮች ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
አርሜኒያ ቀጣይ በምትጀምረው የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የትምህርት ዕድል የኢትዮጵያ ተማሪዎች ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።