ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የክልሉን ሁለንተናዊ ልማትና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ 

ሀረር፣መስከረም 22/2019 (ኢዜአ):- በሀረሪ ክልል በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የክልሉን ሁለንተናዊ ልማትና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት፣ 1ኛ መስራች ጉባዔውን እያካሄደ ሲሆን አቶ ኦርዲን በድሪ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።

በዚህም  ህዝቡንና ክልላችንን ወደ ከፍታና ብልፅግና ለማድረስ መንገድ ጀምረናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በፖለቲካ ፣ በሰላም፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

የዜጎች ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ፣ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ፣የትምህርትና ጤና አገልግሎት ጥራት እንዲረጋገጥ መደረጉን ጠቁመው  በኮሪደር ልማትም ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማን መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።

የሀረር ከተማን በዓለም አቀፍ መድረኮች እውቅና እንድታገኝ ከማስቻል ባሻገር  በግብርናና በሌማት ትሩፋት ዘርፎች  ምርታማነትን በማሳደግ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የክልሉን ሁለንተናዊ ልማትና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

የተመዘገቡ ውጤቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ከማድረግ ባሻገር ለክልሉ እድገት የበለጠ አቅም የሚሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በዕቅድ በመያዝ ተግባራዊ እናደርጋለን  ሲሉም አክለዋል።

ሀረር የሰላም ተምሳሌት እንድትሆንና በክልሉ ፈጣን፣ ፍትሀዊ  ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ የማህበረሰቡን ህይወት የሚያሻሽሉ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ክልሉን በኮሪደር ልማት ለስራ፣ ለኑሮና ለቱሪዝም ይበልጥ ምቹ ለማድረግ ይሰራል ሲሉ አመላክተዋል ።

በክልሉ ፍትሀዊ  የመሰረተ ልማት ስርጭት እንዲኖርና  የዜጎች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከብልሹ አሰራር የፀዱ ፣ይበልጥ ፍትሀዊና ፈጣን እንዲሆኑ በማስቻል የዜጎችን እርካታ ለመጨመር ይሰራል ሲሉም አስታውቀዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም