ቀጥታ፡

የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያን የዲዲጂታል እመርታን የሚያሳልጥ የሰው ሃይል እያፈራ ነው

አዲስ አበባ፣መስከረም 21/2019(ኢዜአ)፡-የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያን የዲጂታል እመርታን የሚያሳልጥ የሰው ሃይል እያፈራ መሆኑን የትምህርት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይለማሪያም ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ ባላት ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በሁሉም መስክ የሀገርን ማንሰራራት የሚያበስር እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ነው።

የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የ50 ዓመታት የምርምር፣ ኢኖቬሽን፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ኢንተርፕርነርሽፕ ጉዞን እና ቀጣይ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።


 

ለሦስት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ማጠናቀቂያም የኢትዮጵያ ተሰጥኦ እና ተውህቦ ማበልፀጊያ ኢንስቲትዩት የቡራዩ ተሰጥኦ ልማት ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸው ባለልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎችን አስመርቋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቡራዩ የልዩ ተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይለማሪያም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለልዩ ተሰጥኦ ወጣቶችን በማሰልጠን የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል የሰው ኃይል እያፈራ ነው።

በትምህርት ቤቱ ሥልጠና የሚሰጣቸው ባለልዩ ተሰጥኦ ወጣቶችም ከፍተኛ የማሰብ፣ የማገናዘብና የመተንተን አቅማቸውን ታሳቢ ባደረጉ መስፈርቶች ተመልምለው የሚሰለጥኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ታዳጊዎች የፈጠራ ክህሎትና ልዩ ተሰጧቸውን በማበልጸግ ችግር ፈቺ የመፍትሔ ውጤቶችን የሚያፈልቁበት ወሳኝ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂዎችም በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው ንድፈ ሃሳብን ከተግባር ተኮር ያቀናጀ ዕውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላትም ታዳጊዎች ክህሎታቸውን የሚያበለጽጉበትን ዕድል በማመቻቸት ቀጣይነት ያለው ሥራ በመሥራት እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ተመራቂ ተማሪዎቹ በበኩላቸው፤ የልዩ ተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት ተፈጥሯዊ ተሰጥኦቸውን በተግባር ልምምድ የታገዘ ሥልጠና የሚያገኙበትን የዕውቀትና ክህሎት ማበልፀጊያ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ማክዳ ወርቅሸት፤ ትምህርት ቤቱ ልዩ ተሰጥኦቸውን የሚያበለጽጉበትን ወሳኝ ትምህርትና ሥልጠና ዕድል ሰጥቶናል ብላለች።

የሥልጠና ቆይታቸውም የልዩ ተሰጥኦ ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማበልጸግ ከዓለም አቀፍ የዲጂታል ተወዳዳሪነትን እንደሚያጎለብትላቸው ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዲጂታል ልማት የቴክኖሎጂ ልዩ ተሰጧቸውን የምናጎለብትበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሮልናል ያለው ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት በተሻለ አበበ ነው።

በአሁኑ ወቅት የክረምት ሥልጠናዎችና ልዩ ልዩ የፈጠራ ማሳያ መድረኮች በርካታ ዕድሎችን በመፍጠር ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች የሚጠቀሙበትን ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጿል።

ወጣቶችም የኢንተርኔት አክሰስንና አዳዲስ ዕድሎችን በመጠቀም የራስን ጥረት ማዕከል በማድረግ አዳዲስ ሶፍትዌሮችን በማልማት ዕድሉን መጠቀም እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም