ዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና አምራች አርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና አምራች አርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው
ዲላ፤ መስከረም 21/2019 (ኢዜአ)፡- የቡና ልማትን በማዘመንና የምርቱን ጥራት በማስጠበቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ዲላ ዩኒቨርሰቲ አስታወቀ።
በዩኒቨርሰቲው 12ኛው ዓለም አቀፍ የቡና ቀን "ቡና የመፍትሔው አካል ነው" በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ነው።
የዲላ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዝዳንት ቶሎሳ ዳዲ (ዶ/ር)፣ በወቅቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለአርሶ አደሩ የተሻሻሉ የቡና ዝርያ በማቅረብና በዘመናዊ መንገድ በማልማት ተጠቃሚ የሚሆንበትን አቅም ማሳደግ ላይ በቅንጅት እየሰራ ነው።
የአየር ንብረት ተጽዕኖን የሚቋቋም የቡና ዝርያን በማስስፋት፣ በቡና ግብይትና ጥራት የግንዛቤ ስራዎችን በማጠናከር የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተከናወኑ ቅንጅታዊ ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ጠቁመዋል።
የቡና ቀን መከበርም ለደጋና ቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የቡና ዝርያዎችን ለማፍለቅና ለማላመድ ለሚደረገው ጥረት ተጨማሪ ልምድ እንደሚያስገኝ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን የብዝሃ ጣዕሞች ባለቤት ናት ያሉት ደግሞ ብሔራዊ የቡና ማህበር ፕሬዝዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) ናቸው።
የቀኑ መከበርም የቡና ልማት ተዋንያንንና የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ማህበሩ ቡና ከማሳ እስከ ዓለም ገበያ ጥራቱን ጠብቆ በማዘጋጀት የዘርፉን ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳካትም አመራረቱን ማዘመንና በምርምር ማስደገፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በተለይ እሴት በመጨመርና የኢትዮጵያን ቡና ዓለም አቀፍ ስያሜን በማጉላት ረገድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ የፍራፍሬ ዴስክ ሃላፊ አቶ ተገኝ ኢረና በበኩላቸው ቡና ከኢኮኖሚ ምንጭነት ባለፈ የማህበራዊ ትስስርና የአከባቢ ጥበቃ መሰረት ነው ብለዋል።
ለስኬቱም የቡና ልማትና የግብይት ሥርዓት በማሻሻል የአርሶ አደሩንና የሀገርን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።
የቡና ግብይትን ውጤታማ በማድረግ አርሶ አደሩ ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የገበያ ትስስር መፍጠርና በጥራት አዘጋጅቶ ለገበያ እንዲያቀርብ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ በምሁራን በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ምክክር የተደረገ ሲሆን የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም አልሚዎችና ላኪዎች ተሳትፈዋል።