ቀጥታ፡

ከጠንካራ ርዕይ ወደ ላቀ ሀገራዊ ስኬት - አዲሱ የመንግስት ምስረታ

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥና የላቁ ሀገራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ ለሚያስችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለው እንደሚጠብቁ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የያዘችውን ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ እውን ማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በውጤታማነት በማከናወን እንዲሁም ትልልቅ ሀገራዊ ሁነቶችን በማዘጋጀት በኩል በርካታ ድሎችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

በውጤታማነት ከተገበረቻቸው ታላላቅ ሀገራዊ ሁነቶች መካከል በ2018 ዓም አሳታፊ እና አካታች በሆነ መልኩ የተከናወነው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እና በምርጫው በንቃት የተሳተፈው ህዝብ እና የተገኘው ድል ተጠቃሽ ናቸው።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች በመሳተፍ ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ጽኑ መሻት በተግባር አሳይተዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብ ይሁንታን ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ በመጪው ሰኞ መስከረም 25/2019ዓም መንግሥት ይመሰርታል፡፡

ኢትዮጵያ አሳታፊ እና አካታች ምርጫ ማካሄዷን ከሚያረጋግጡ ጉዳዮች መካከል የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በየክልሎች ምክር ቤቶች መቀመጫ ያሸነፉባቸውን ድምጾች ማግኘታቸው ይጠቀሳል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን፣ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለውን ጽኑ ፍላጎት በምርጫ ካርዱ በመወሰን የአዲሱን መንግሥት ምስረታ በጉጉት እየተጠባበቀም ይገኛል።

የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስታወቁም ይታወቃል።

ኢዜአ የሚመሰረተው አዲስ መንግሥት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ምን ምን ተግባራት ላይ ቢያተኩር ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ አስተዋጽኦ ያበረክታል በሚለው ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል እንደሻው ጸጋየ እንደገለጹት፤ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማፋጠን የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

ከእነዚህ መካከልም ገበያውን ለማረጋጋት ቀደም ሲል የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራትን ይበልጥ እንዲጠናከሩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለው እንደሚጠብቁም አክለዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መታሰቢያ ጠብቀው፤ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ህዝብን በማስተባበር ሀገር የሚጠቅም ስራ ለመስራት የገባውን ቃል በተግባር ያሳያል ብላ እንደምትጠብቅ ገልጻለች።

በተጨማሪም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች በውጤታማነት እንዲቀጥሉ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ህዝብን በማሳተፍ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብላለች፡፡

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ለገበያ መረጋጋት፣ ለቤት አቅርቦት እና ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና ትኩረት በመስጠት ይሰራል ብሎ እንደሚያምን የተናገረው ደግሞ ሙደሲር ሙዘይን ነው፡፡

በቀጣይም መንግሥት የስራ ዕድል የሚፈጠርባቸውን መስኮች በማስፋት ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባውም ነው ያመላከተው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም