ቀጥታ፡

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የአካባቢ ጥበቃ ሕግጋት ትግበራ ውጤታማነትን እያጎለበተ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦የጽዱ ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ የአካባቢ ጥበቃ ሕግጋት ትግበራ ውጤታማነትን በማጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።

በተለይም የከተሞችን ሁለንተናዊ ጽዳትና ውበት ከማሻሻል ባሻገር ለአካባቢ ጥበቃና ሥነ-ምኅዳር ድኅንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የጽዱ ኢትዮጵያ ተነሳሽነት ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ዘመናዊ ምኅዳርን በማጎናጸፍ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻና መሰል ውጤታማ የልማት ሥራዎችን የሚያፋጥን አስቻይ ምኅዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንም የሕብረተሰብ ተሳትፎን በማሳደግ የጽዱ ኢትዮጵያን ግብ የሚያሳካ የአካባቢ ጥበቃ፣ የጽዳትና ውበት ባህልን የሚያጎለብት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር "ውበት ይንቃ፤ ብክለት ይብቃ" በሚል መሪ ሀሳብ ለስድስት ወራት የብክለት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መከናወኑን አስታውሰዋል።

በሁለተኛው ዙር ደግሞ "ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ" በሚል መሪ ሀሳብ የጽዳት ባህልን ማጠናከር የሚያስችል መሰረት መጣል እንደተቻለ አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሰኔ እስከ መስከረም ለ3 ወራት የሚቆይ 3ኛ ዙር ''የጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ'' ሀገር አቀፍ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን አንስተዋል።

በየዓመቱ የሚካሄዱት የጽዱ ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄም የማኅበረሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ በማጎልበት ተቋማት በብክለት መከላከል ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ እያደረገ ነው ብለዋል።

መርሐ ግብሩም የአካባቢ ጥበቃ ሕግጋትና መመሪያዎችን ሙሉ በሙሉ በውጤታማነት በማስፈጸም ለአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማጠናከር በቀጣይም ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥና ብክለትን ለመከላከል የተቀናጁ የአካባቢ የጽዳትና ውበት ጥበቃ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም