ብሔራዊ የወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ስትራቴጂ የፋይናንስ አካታችነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ስትራቴጂ የፋይናንስ አካታችነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ስትራቴጂ የፋይናንስ አካታችነትን በማንበር ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ራዕይ ባላት ኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም 2026 ተጠናቋል።
በመድረኩም ከ2026 እስከ 2030 የሚቆየው የመጀመሪያው የአምስት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከተጀመረ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል።
በተደራጀ ሕግና የቁጥጥር ሥርዓት የተደገፈ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት በፊት አገልግሎቱ እየተሻሻለ መጥቶ በባንክ ዘርፉ ከተሰበሰበው የቁጠባ ገንዘብ 10 በመቶ የሚሆነው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፍ መሰናክሎች በመፍታት አካታች የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት፣ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል የወለድ ነፃ የፋይናንስ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ስትራቴጂ ሀገራዊ የሸሪዓ አስተዳደር መፍጠር፣ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት ማሳደግ፣ የወለድ ነፃ አገልግሎት የሚፈልጋቸው ሕጎችና አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት የምታገኘው ጥቅም በቂ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ፍሬዘር፤ ኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ምቹ ገበያና የመንግሥት ቁርጠኝነት አለ ብለዋል።
በብሔራዊ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት የፋይናንስ አካታችነት ላይ ተጨባጭ ውጤት በማምጣት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያሳደግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የመንግሥት ጽኑ ፍላጎትና ሰፊ ገበያ በማስተሳሰር ዘርፉን የበለጠ ማሳደግና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጎልበት ያስችላል ብለዋል።
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የአልሁዳ ኢስላሚክ ባንክና ኢኮኖሚክስ ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሐመድ ዙባይር በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፍ የኢስላሚክ ባንኮች የወለድ ነፃ ፋይናንስ 6 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ብለዋል።
በ120 ሀገራት ከ7 ሺህ በላይ የኢስላሚክ ባንኮች እንዳሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ማዕከል መሆን የሚያስችል አቅም እንዳላት ተናግረዋል።
የወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎትን በተመለከተ በአንዳንድ ሀገራት የመንግሥት ቁርጠኝነት አለ በገበያው ላይ ፍላጎት የለም፤ በሌሎች ደግሞ ፍላጎት አለ የመንግሥት ቁርጠኝነት የለም ብለዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ሁለቱንም አስተሳስራ የያዘችው በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የተሻለ ዕድል ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሊካ በድሪ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ስትራቴጂ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እርምጃ ብለውታል።
በኢትዮጵያ በተበታተነ መንገድ ይሰጥ የነበረውን የወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ወጥ በሆነ፣ በተደራጀና በሸሪዓ አስተዳደር እንዲመራ በማድረግ በደንበኞች ዘንድ እምነትን ያሳድራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የነፃ ወለድ ፋይናንስ አገልግሎት ስትራቴጂ አልነበራትም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ለባንኩ ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።