ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋገጡ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቤርዴ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ንድያሜ ዲዮፕ ተገኝተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የበጀት ድጋፎችን ጨምሮ እያደረገ ለሚገኘው ዘላቂ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እየተገበረች የሚገኘውን የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳን አስመልክቶ ለዓለም ባንክ አመራሮች ገለጻ አድርገዋል።

በዚህም የሀገር ውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅም፣ የንግድ ስራ ምቹነት እና የግል ባለሀብቶች በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማደጉን አመልክተዋል።

የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቤርዴ በኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ የተገኙ ለውጦችን አድንቀዋል።

መንግስት የግሉ ዘርፍን ማዕከል ያደረገ እድገት እንዲኖር እና የስራ እድል ፈጠራ ማሳደግን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የታዩ ተጨባጭ ለውጦችን አንስተዋል።

የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የሀገሪቱን የቅድሚያ የልማት ትኩረቶች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተለይም በአዲሱ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ አጋርነት ማዕቀፍ ስር የግሉ ዘርፍ በባለቤትነት ወደ ሚመራው የእድገት ምዕራፍ ለመሸጋገር በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳለም አንስተዋል።

ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት ውይይት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ማድረግ፣ የግብርና ዘርፉን በቴክኖሎጂና በግብዓት ማስተሳሰርና ማሳደግ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓትን መዘርጋት፣ እንዲሁም የውህ ሀብትን አጠቃቀምና ተደራሽነት ማረጋገጥ ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከውጭ የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም የምታስችላትን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማግኛ መንገዶችን ማስፋት የሚገባ መሆኑን ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የልማት ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን በተዘጋጀው የልማት ዝግጁነት ማዕቀፍ ውስጥ በቁርጠኝነት ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።

ማዕቀፉ ለህዝብ ቀጥተኛ ተጠቃሚነት የሚውሉና ተጨባጭ ለውጥ የሚያስገኙ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

ውይይቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በዓለም ባንክ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይህም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን፣ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ማለፍ እንዲሁም የግል ዘርፍ እድገቱን መምራቱ የሚያስገኘውን ዘላቂ ዕድገት እውን ለማድረግ ጠንካራ የጋራ ቁርጠኝነት እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም