የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በሁሉም መስክ ትርጉም ያለው ውጤት አስገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በሁሉም መስክ ትርጉም ያለው ውጤት አስገኝቷል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በሁሉም መስክ ትርጉም ያለው ውጤት ማስገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ራዕይ ባላት ኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም 2026 ተጠናቋል።
በመድረኩም ከ2026 እስከ 2030 የሚቆየው የመጀመሪያው የአምስት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዓለም ኢትዮጵያን የሚያይበት መንገድ በመሠረታዊነት ተለውጧል።
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮቿን በማስፋፋት በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና አይ.ሲ.ቲ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎች አብዮት መፍጠሩን በማንሳት፤ ማዕድን ወሳኝ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ መምጣቱን ገልጸዋል።
የዲጂታል ግብይት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፤ የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በሁሉም መስኮች ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም ወደፊት እየተጓዘ ነው ያሉት ገዥው፤ ኢኮኖሚው በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንዳለ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያው በወርቅ የወጪ ንግድ አስደናቂ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸው፤ በመደበኛውና በተይዩ ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ልዩነት ጠቧል ብለዋል።
ሀብትን በመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት ፈሰስ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል፤ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችትም ማደጉን ገልጸዋል።
ሪፎርሙ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግና ቱሪዝምን በማስፋት ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።