የኢትዮጵያ ከተሞች ትንሳኤ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከተሞች ትንሳኤ
በመጽሔት አንለይ
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ ሰንቃ እየተጋች የምትገኝ የገናና ሥልጣኔና የታሪክ ማኅደር፣ የቱባ ባህልና የሕብረብሔራዊ አንድነት ካስማ ናት። በክትመትና ከተሜነት ሥልጣኔም የሺህ ዘመናት የሥልጣኔ ዐሻራ በጉያዋ ታቅፋለች።
የከተሜነት አመጣጥ የሁሉም ክፍለ አህጉራት አባል ሀገራት የጋራ ታሪክ ነው። አፍሪካም ከጥንት ጀምሮ የተደራጁና የደረጁ የከተማ ሥልጣኔዎች የታሪክ መናኸሪያ መሆኗን ድርሳናትና መዛግብት ያስረዳሉ። ጥንታውያኑ የአክሱም፣ ጎንደርና ሐረር በኢትዮጵያ፤ ቲምቡክቱ፣ ካኖና ኦዮ በምዕራብ አፍሪካ፤ ግሬት ዚምባብዌ በደቡብ አፍሪካ፤ ኪልዋና ሞምባሳ በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የአፍሪካ ከተሜነት ሥልጣኔ ረጅም ታሪክ እንዳለው አስረጂዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅትም አፍሪካ የዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ማራኪ፣ ውብና ጽዱ ገጽታን የተላበሱ ከተሞችን መገንባቷን ኪጋሊ፣ ራባት፣ ኮቶኑ፣ ታንጀር፣ ማራካሽ፣ አቡጃ፣ ጋቦሮኔ፣ ዊንድሁክ፣ ኬፕ ታውን እና መሰሎችም ሁነኛ አብነቶች ናቸው።
በአፍሪካ ከተማና የከተሜነት ሥርዓትና ምኅዳር ከጉስቁልና ወደ ተሻለ የልዕልና መንገድ የሚያመራበት ከፍተኛ ዕድል አለው። ይህም የአህጉሪቷ የከተማ ሕይወት በተሰናሰለ መሰረተ ልማት የሚመራና ብሩህ ተስፋ ያለው መሆኑን ያስረዳል።
ኢትዮጵያ፤ የጥንታዊ ሥልጣኔ ዐሻራ ያረፈባቸው ከተሞች ሀገር!!
የኢትዮጵያ የከተሜነት ዐሻራ ከጥንታዊ የሥልጣኔ ታሪኳ ጋር ተሰናስሎ የቀጠለና ያልተቋረጠ ሂደት ነው። አክሱም የንግድና የሥልጣኔ ማዕከል፣ ሐረር የንግድ፣ የባህልና የኃይማኖት መናኸሪያ ሆና ቆይታለች። ጎንደር ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ አስተዳደር ማዕከል ሆና በማገልገል ታሪክ ሰርታለች፤ ሰንዳለችም።
አዲስ አበባ ደግሞ በዘመናዊ ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆን የኢትዮጵያ ዘመናዊ የከተሜነት ጉዞን መርታለች፤ እየመራችም ይገኛል። የከተማ ዕድገት ፈጣን ሲሆን ተጓዳኝ ጫናዎችም ይመጣሉ። የዓለም ባንክ በአዲስ አበባ ላይ ያደረገው የከተማ ጽናት ጥናት ፈጣን የከተማ ዕድገት ከጎርፍ፣ ከውሃ እጥረት፣ ከትራንስፖርት፣ ከሥራ አጥነትና ከማህበራዊ ተጋላጭነት ጋር የሚያያዙ ጫናዎችን እንደሚያመጣ ያመለክታል።
ከዓመታት በፊትም አዲስ አበባና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በመሰረተ ልማት ክፍተትና በእርጅና ብዛት የሚያቃናቸውን የለውጥ አብዮት ሲጠባበቁ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ የከተማ ትንሳኤ ትርጉሙ የከተሞችን ፊት በማስዋብ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ መመልከት ይቻላል። የኑሮ ጥራትን፣ ምርታማነትን፣ የሥራ ዕድልን፣ የመጓጓዣ ቅልጥፍናን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የሕዝብ ተሳትፎን አስናስሎ የሚጓዝ ሂደትን መፍጠር ይጠይቃል።
ከቢሮ ጽዳትና ውበት ወደ የኢትዮጵያ ከተሞች የትንሳኤ ብስራት፤ ከእርጅና ወደ ልዕልና!!
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የመደመር መንግሥት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጽዳትና ውበት ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ይገባል የሚል ጽኑ አቋምን አብስሯል። በዚህም በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የቢሮ ዕድሳት ማራኪ የሥራ ከባቢን መፍጠር አስችሏል።
በቢሮ ዕድሳት የተመዘገበው እመርታዊ ውጤትም የኢትዮጵያ ከተሞችን የውበት አክሊል የሚያጎናጽፍ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የሚገነባበትን ዕድል ፈጥሯል። ይህም የኢትዮጵያ ከተሞችን በማፍካት የከተሜነት የአኗኗር ምኅዳር ዝማኔን የውበት አክሊል አቀዳጅቷል።
ይህ ለውጥም የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የተደራሽነት አድማስን በበርካታ ከተሞች የኮሪደር፣ የፓርኮች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የቅርስ ጥበቃና ማራኪ የሕዝብ መዝናኛ ግንባታ በማስፋፋት የኢትዮጵያን ልክና መልክ ገልጠዋል።
የአዲስ አበባ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች እመርታም የሕዝብን የከተሜነት የአኗኗር ሥርዓት ከከተማ ሕይወት ጋር የማስተሳሰር ተምሳሌቶች ናቸው። በክልሎችም ተመሳሳይ የከተማ ውበት፣ የቱሪዝም፣ የቅርስና የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች ልማት በስፋት ተከናወነዋል፤ እየተከናወኑም ነው።
የዚህ ሂደት ዋና እሴት ውበት ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል። የተሻለ የከተሜነት ምኅዳር ምቹ የንግድ፣ ቱሪዝም፣ መዝናኛ፣ ማህበራዊ ትስስርና የከተማ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው። ይህም የከተሞችን የኢኮኖሚ መነቃቃት የሚያሳልጥ የመሰረተ ልማት ግንባታና የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ገበታ ለሸገር ከገለጣት አዲስ አበባ የተሻገረው፤ የገበታ ለሀገርና ለትውልድ እመርታ!!
የኢትዮጵያ ከተሞች ለውጥ ዘላቂ የከተሜነት ሽግግርን የማፋጥን መሰረት እየጣለ ይገኛል። የአዲስ አበባን ልማት ከክልል ከተሞች፣ የከተማ ልማትን ከገጠር ምርት፣ ቱሪዝም ከቅርስ ጥበቃ፣ የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራን ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር አሰናስሎ ማስቀጠልም ቀጣይነት ያለው ሥራን ይጠይቃል።
በዚህ አቅጣጫ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ በተሰኙት የልማት ሐሳቦች የተገነቡ ማራኪ የልማት ፕሮጀክቶች የተፈጥሮ፣ የባህል፣ የቱሪዝምና የሕዝብ መዝናኛ ሃብቶችን ወደ ኢኮኖሚያዊ እሴት መቀየር ያስቻሉ ናቸው።
በአዲስ አበባ በገበታ ለሸገር የተገነቡት የአንድነት፣ ወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች የመዲናዋን ስምና ግብር ከገለጡት የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር ተዳምረው ማራኪ የመስህብ መዳረሻ ምኅዳርን ፈጥረዋል። ይህም የከተማ ልማት ከውበት ወደ ምርታማነት መሻገሩን የሚያሳይ ወሳኝ ብስራት ነው።
በገበታ ለሀገር የተገነቡት የጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሐላላ ኬላ፣ ኮይሻና ሌሎች የኢኮኖ ቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችም የኢትዮጵያን ጥንታዊ የከተሜነት ሥልጣኔ ከዘመናዊ የዓለም ከተሜነት ጋር ያሰናሰሉ የልማት ብስራቶች ናቸው። ፕሮጀክቶቹም የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም በተግባር አስመስክረዋል።
የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችም የተገነቡት የሎጎ ሐይቅ፣ ዓርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት፣ ኒን ሊ ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ፣ የሸበሌ ሪዞርት፣ ደንዲ ኢኮ-ሎጅ እና ሌሎችም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የቱሪዝም ዘርፍ የማንሰራራት ጉዞ በማነጽ የብልፅግናን ብርሃን ፈንጥቀዋል።
የከተማ እመርታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኘዎችን የስበት ማዕከል እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የተደራጀ ከተማም የተመቻቸ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳርን በመፍጠር የምርታማነት አቅም ያጎለብታል። የከተማ መሰረተ ልማት ደግሞ ምርታማነትን ያሳድጋል። ሦስቱ ሲጣመሩም ከተማ የኢኮኖሚ ሞተር ትሆናለች።
የኢትዮጵያ ከተሞች የወደፊት ሕልም!!
የከተሞች ትንሳኤ የሚለካው በአዲስ እሳቤ ተሰናስለው በሚገነቡ መሰረተ ልማቶች መሆኑ እሙን ነው። የከተማ ልማት ሲቀጥል ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት፣ ውሃና ፍሳሽ፣ የቆሻሻ አያያዝ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ የአካባቢ ጽናትና የሥራ ዕድል ፈጠራን አብረው መሄድ አለባቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2025 የከተማ ትንበያም የከተማ ልማትን ከሁሉን አቀፍ፣ አስተማማኝ፣ ጽኑና ዘላቂ የከተማ ሕይወት ጋር አቆራኝቶ መምራት እንደሚስፈልግ ያመላክታል። ይህም ለኢትዮጵያ ከተሞችን ማስዋብ እና መሰረተ ልማትን ማስፋፋት አንዱ ክፍል ሲሆን፤ የከተማን ኢኮኖሚ ማሳደግ፣ ሥራ መፍጠር፣ ለዜጎች የተሻለ የኑሮ ዕድል መፍጠርና የከተሞችን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስን ሽግግርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ትምህርት ይሰጣል። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ከተሞች የነገ ሽግግራቸውን የሚያፋጥን ምቹ መደላድል ፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች ትንሳኤ፤ ከእርጅና ወደ ልዕልና
የዓለም ከተሞች የሚያመሳስላቸው አንድ የታሪክ እውነት አለ። ከተማ በአንድ ቀን የሚገነባ ሳይሆን በትውልድ ቅብብሎሽ በሚደረግ የዕውቀት፣ የሥራ፣ የዕቅድና የፈጠራ ሥራ የሚቀጥሉ ናቸው። ኢትዮጵያም ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐረር እስከ አዲስ አበባ ረጅሙ የከተሜነት ታሪክ አላት። ዛሬ የተከፈተው አዲስ ምዕራፍም የአረጁና የኮሰመኑ ከተሞች አዲስ የከተሜነት ቅርፅና መልክ የሚይዙበትን ዕድል ፈጥሯል። ይህም አዳዲስ ከተሞችን በተቀናጀ ዕቅድ በመገንባት ከተሞችን የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር እያደረገ ነው።
በዚህም በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ድሬ ዳዋ፣ ሐረር፣ አዳማ፣ ባሕር ዳር፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ፣ ሶዶ፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ነቀምትና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችን ከእርጅና ወደ ልዕልና የተሸጋገሩበትን ወርቃማ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
የአዲስ አበባ፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ-መንግሥትና ሌሎች ከተሞች የቅርስ ዕድሳቶችም ታሪክን ለትውልድ በማሻገር ከተሞቹን ተደማሪ የውብት አከሊልን አቀዳጅቷል። የከተሞቹ የኮሪደር ልማትም ከእርጅና ወደ ልዕልና የሚለው ሐሳብ የከተሞችን የቆዩ መዋቅራዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ችግሮች በአዲስ ዕይታ የመፍታት የሽግግር ተምሳሌት ነው።
የኢትዮጵያ ከተሞች ዛሬ የሚገኙበት የለውጥ ሂደትም በዚህ ሰፊ የዓለም የከተሜነት ጉዞና ሥልጣኔ የሚታይ ነው። ጥንታዊ የከተሜነት ሥልጣኔን የወረሰች ኢትዮጵያም የወደፊቱን የከተሜነት ምኅዳር በዕውቀት፣ ፈጠራ፣ መሰረተ ልማት፣ በባህልና በሰው ኃይል መቅረፅ የሚያስቻለትን መሰረት በመጣል ወሳኝ አቅም ገንብታለች።